ኢሳት (ታህሳስ 4 ፥ 2009)
ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለየዩ የአለማችን ሃገራት በመገባደድ ላይ ባለው የ2016 የፈረንጆች አም ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞች ቁጥር መጨመሩን የዘንድሮውን አመታዊ ሪፖርት ማክሰኞች ይፋ ያደረገው ኪሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆዎርናሊስትስ (CPJ) አስታወቀ።
በአፍሪካ ካሉ ሃገራት መካከል ጋዜጠኞችን በማሰር በሶስተኛ ድረጃ ላይ የተቀመጠችውን ኢትዮጵያ በተያዘው አመት 16 ጋዜጠኞች ለእስር ዳርጋ እንደምትገኝ በጋዜጠኞች መብት መከበር ዙሪያ የሚሰራውና መቀመጫውን በዚሁ በአሜሪካ ያደረገው ድርጅት ገልጿል።
ቱርክ 81፣ ቻይና 38፣ ግብፅ 25፣ ኤርትራ 17፣ ኢትዮጵያ 16 ጋዜጠኞችን ለእስር በመዳረግ በአለም ካሉ ሃገራት ግንባር ቀደም ሆነው በቅድመ ተከተል ተቀምጠዋል።
በኢትዮጵያ የሽብርተኛ አዋጅ ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ በርካታ ጋዜጠኞች ለእስር ሲዳረጉ መቆየታቸውን ያወሳው CPJ ፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገሪቱ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞና ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለእስር የሚዳረጉ ጋዜጠኞች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉ ታውቋል።
ረዥም የእስር ቅጣት ከተላለፈባቸው ጋዜጠኞች በተጨማሪ ያለምንም ክስ ለእስር ተዳርገው የሚገኙ ጋዜጠኞች በእስር ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለእስር የሚደረጉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።
ከ16ቱ ጋዜጠኞች አንዱ የሆነውና ከሁለት አመት በፊት የሶስት አመት የእስር ቅጣት ተላልፎበት የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በእስር ላይ ከሚገኝበት የዝዋይ እስር ቤት ባለፈው ሳምንት የለም መባሉን መዘገባችን ይታወሳል።
የጋዜጠኛውን ጉዳይ በመከታተል ላይ የሚገኙ አካላት የጋዜጠኛው ቤተሰቦችና የቅርብ ጓደኞች ወደ ተለያዩ እስር ቤቶች በመሄድ ፍለጋን ቢያካሄዱም እስከ ማክሰኞ ድረስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ያለበት ቦታና ሁኔታ አለመታወቁን ለመረዳት ተችሏል።
በአለም ዙሪያ በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸሙ እስራትና እንግልቶችን አስመልክቶ የ2016 አም ሪፖርቱን ያወጣው ሲፒጄ፣ በዘንድሮው አመት 259 ጋዜጠኞች በ32 ሃገራት ለእስር መዳረጋቸውን አስታውቋል።
በተያዘው አመት ለእስር የተዳረጉ የጋዜጠኞች ቁጥር ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ60 ጋዜጠኞች ጨምሮ የተገኘ ሲሆን፣ ይኸው ቁጥር ከ25 አመት በኋላ ሪከርድ ተደርጎ ተመዝግቧል።
በአፍሪካ ግብፅ፣ ኤርትራ፣ እና ኢትዮጵያ በርካታ ጋዜተኞችን ለእስር በመዳረግ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ተቀምጠዋል።