ለአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ኢትዮጵያውያን ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ተመድ ገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 4 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ በአዲስ መልክ የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመከላከልና በሃገሪቱ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ድጋፍ ለማቅረብ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞች ይፋ አደረገ።

ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች ተከስቶ የነበረው የድርቅ አደጋ ዕልባት ሳያገኝ ከሁለት ወር በፊት አዲስ የድርቅ አደጋ መከሰቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎቱ እንዲጨምር ማድረጉ ታውቋል።

በፈረንጆቹ 2017 አም በኢትዮጵያ ተከስቶ ላለው የድርቅ አደጋ የሚያስፈልገው 900 ሚሊዮን ዶላር ወደ ስድስት ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች የምግብ ድጋፍ ለመቅረፍ ያስፈልጋል። የዘንድሮው የእርዳታ ድጋፍም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ44 በመቶ ይጨምራል ተብሎ ተገምቷል።

ከስድስት ሚሊዮን ሰዎች በተጨማሪ 1.2 ሚሊዮን ህጻናትና በዕርግዝና ላይ ያሉ እናቶች የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦቶች እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያ በሚያስፈልጋት አለም አቀፍ ድጋፍ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

በፈረንጆች አዲስ አመት ከ300 ሺ የሚበልጡ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት ይጋለጣሉ ተብሎ ስጋት መኖሩንም ድርጅቱ አሳስቧል።

በሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ስር የሚገኙ በርካታ ዞኖች አዲስ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል። በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት መሞታቸውንም አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በመግለጽ ላይ ናቸው።

ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ተጋልጠው እንደነበር ይታወሳል።

የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለተረጂዎች የሚያስፈልገውን የምግብ አቅርቦት ለማድረግ ጥረት ቢያደርግም በቂ የገንዘብ ልገሳ ባለመገኘቱ ምክንያት ችግሩ አለመቀረፉ ተመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት 9.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለምግብ ድጋፍ ተጋልጠው ይገኛሉ፣ አዲስ የተከሰተው የድርቅ አድጋ የተረጂዎችን ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል ተብሏል።

ባለፈው አመት በኢትዮጵያ የተከሰተው የድርቅ አደጋ የግብርና ምርት ላይ ተፅዕኖን በማሳደር የሃገሪቱ የወጪ ንግድ እንዲያሽቆለቁል ማድረጉን የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሶስት በመቶ አካባቢ መቀነስን አሳይቶ የነበረው የግብርና የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲቀንስ ማድረጉንም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የአለም ባንክ በበኩሉ በሃገሪቱ ያለው አለመረጋጋትና የውጭ ንግድ መቀነስ በቀጣዩ አመት ቀጣይ በመሆን በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ሊያሳድር እንደሚችል ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርቱ አሳስቧል።