አርበኞች ግንቦት ሰባትንና የኦርሞ ነጻነት ግንባርን (ኦነግን) ተቀላቅለዋል የተባሉ አምስት ወታደሮችና ግለሰቦች ተከሰሱ

ኢሳት (ታህሳስ 3 ፥ 2009)

የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመክዳት አርበኞች ግንቦት ሰባትና የኦርሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግን) ተቀላቅለዋል የተባሉ አምስት ወታደሮችና ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው። የአየር ሃይል የደህንነት ሃላፊን ለመግደል በደህንነት መዋቅሩ ውስጥ ሲሰሩ እንደነበርም ተመልክቷል።

የፌዴራል አቃቤ ህግ የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ያቀረበባቸው እነዚሁ ተከሳሾች ሁለቱ የአገር መከላከልያ ሚኒስቴር አባላት የነበሩ ሶስቱ ደግሞ የአርበኞች ግንቦት ሰባትና ኦነግ አባላት መሆናቸው በሃገር ውስት ያሉ መገኛና ብዙሃን ዘግበዋል።

ከቀናት በፊት ክስ የቀረበባቸው አምስቱ ተከሳሾች በደብረ ዘይት ከተማ የአየር ሃይል ደህንነት ሃላፊን ለመግደል ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም የቀረበባቸው ክስ ያመልክታል።

አወል አባጊዳና ሰይድ መሃመድ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እንደነበሩ የገለጸው ከሳሽ አቃቤ ህግ ሰይድ መሃመድ አንዷለም ያሲንና፣ ሰሚራ አማን የተባሉት ተከሳሾች ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሚያ ክልል እንዲሁም የሰሜን ሱዳን ነዋሪዎች መሆናቸውን በክስ ቻርጁ  አቅርቧል።

ተከሳሾቹ በሰሜን ሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ለአርበኞች ግንቦት 7 እንዲሁም ለኦነግ አባላትን በመመልመልና የሽብርተኛ ድርጊትን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የፌዴራሉ ከሳሽ አቃቤ ህግ አስታውቋል።

ከተከሳሾቹ መካከል የኦሮሞያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪ ነው የተባለው አንዷለም ያሲን በደብረ ዘይት ከተማ እና በተለያዩ ቦታዎች ለሚገኙ ሌሎች አባላት በተለይ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲመለምሉ መመሪያ ሲያስተለልፍ ነበር ተብሏል።

ይሁንና ተከሳሹ ትዕዛዝ አስተላልፈላቸዋል ስለተባሉ ሌሎች አባላት የተሰጠ ዝርዝር መርጃ የሌለ ሲሆን፣ የአየር ሃይል ደህንነት ሃላፊን ለማስገደል ለሌሎች አካላት ተልዕኮ በመስጠት በመንቀሳቀስ ላይ እያለ በቁጥጥር ስር መዋሉን አዲስ አበባ የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።

ሌሎች ተከሳሾቹ ከግንቦት ወር 2008 አም እንቅስቃሴ እንደነበራቸው በክሱ ቢያመለክትም በቁጥጥር ስር የዋሉበት ቀንም ሆነ አካባቢ አልተገለጸም።