አሜሪካ አንድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ መወሰኗን ይፋ አደረገች

ኢሳት (ታህሳስ 3 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ባለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ስጋቷን ስትገልጽ የቆየችው አሜሪካ አንድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ መወሰኗን ሰኞ ይፋ አደረገች።

የዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብቶች ረዳት ሚኒስትር ቶም ማሊኖውስኪ የሚመራ የልዑካን ቡድን ከረቡዕ ጀመሮ በአዲስ አበባ የአራት ቀን ጉብኝት እንደሚያደርግ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ የአራት ቀን ቆይታ የሚኖራቸው ቶም ማሊኖውስኪ በሰብዓዊ መብቶችና በዴሞክራሲ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ለመረዳት ተችሏል። malinowski

ረዳት ሚኒስትሩ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ከሚያደርጉት ምክክር በተጨማሪ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ከሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተገናኝተው በወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

አሜሪካ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ ሃገሪቱ በኢትዮጵያ ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ስጋቷን ስትገልጽ የቆየች ሲሆን፣ ዜጎቿም ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያን ተግባራዊ አድርጋ ትገኛለች።

በቅርቡ ለእስር የተዳረገጉትን የዶ/ር መረራ ጉዳይና ድርጊት በመቃወም አሜሪካ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ መንግስት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አመራሩ የታሰሩበት ሁኔታ ግልጽ እንዲደረግ ጥያቄን አቅርበዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈዋል ተብለው ለእስር የተዳረጉት ዶ/ር መረራ ጉዲና ፍርድ ቤት ቀርበው የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ እንደተጠየቀባቸው መዘገባችን ይታወቃል።

አብረዋቸው የታሰሩት ሁለት ዘመዶቻቸው ከቀናት እስራት በኋላ የታሰሩትበት ምክንያት ሳይነገራቸው መለቀቃቸውም ይታወቃል።