የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ስጋት ማሳደሩ ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 3 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ያለው አለመረጋጋትና ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ስጋት ማሳደሩ ተገለጸ።

በተለይ አየር መንገዱ በአንጎላ እና ናይጀሪያ ሃገራት ያለው ሰፊ የጉዞ እንዲሁም የትኬት ሽያጭ ገበያ ባለፉት በርካታ ወራቶች መቀዛዝቅዝ ማሳየቱን ብሉምበርግ የተለያዩ መርጃዎችን ዋቢ በማድረግ ሰኞ ለንባብ አብቅቷል።

በእነዚሁ ሁለት ሃገራት ብቻ ከትኬት ሽያጭ ከ200 ሚሊዮን ዶላር (ከአራት ቢሊዮን ብር) በላይ ያልተከፈለ እዳ መኖሩን የዜና ወኪሉ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል። ethiopian-airlines

ይኸው የልተከፈለ የቲኬት ሽያጭ እዳ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የፋይናንስ አቅም ላይ ተፅዕኖን አሳድሮ የሚገኝ ሲሆን፣ ድርጅቱ ያልተከፈለ ገንዘቡን ለማስመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ታውቋል።

በአፍሪካ ካሉ አየር መንገዶች አንጋፋና ትርፋማ እንደሆነ የሚነገረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው በጀት አመት 18 በመቶ የትርፍ እድገት ማስመዝገቡን በመግለጽ የተለየ መቀዛቀዝ እንዳልተስተዋለ ምላሽን ሰጥቷል።

ይሁንና ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በማድረግ የአውሮፓ ሃገራት ዜጎቻቸው ወደ ሃገሪቱ እንዳይጓዙ ሲያወጡ የነበረው የጉዞ ማሳሰቢያ በአየር መንገዱ ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ታውቋል።

የአለም አቀፍ ትራንስፖርት ማህበር በበኩሉ በአፍሪካ ያሉ አየር መንገዶች በተያዘውና በቀጣዩ አመት በአለም ብቸኛ ትርፍን የማያገኙ ኩባንያዎች እንደሚሆኑ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ማስፈሩን ብሉምበርግ የዜና ወኪል በዘገባው አስነብቧል።

በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽን የሰጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በሃገሪቱ ያለው አለመረጋጋት በድርጅቱ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ የለም ሲሉ ማስተባበያን ሰጥተዋል።

ይሁንና ከ500 ለሚበልጡ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ህዝባዊ ተቃውሞ በበርካታ ተጓዦች ዘንድ ፍርሃትና ጥርጣሪን አሳድሮ እንደሚገኝ የዜና አውታሩ አመልክቷል።

ባለፈው ወር የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው የጉዞ ማሳሰቢያ ተከትሎ በርካታ የሃገሪቱ አስጎብኚ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርጉ የነበረን የጉብኝት ፕሮግራም መሰረዛቸው ይታወሳል።

በዚሁ ዕርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ጉዞዓቸውን ወደ ሌላ ሃገር ማድረጋቸውን ዘጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል።