ኅዳር ፴ (ሠላሳ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደርግ ስርዓት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት እና ጠቅላይ ሚንስርነት ሆነው ያገለገሉት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ያዴሳ በተወለዱ በ77 ዓመታቸው ህዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
በ1932 ዓ.ም በቀድሞው ሸዋ ክ/ሃገር አንቦ ከተማ ውስጥ የተወለዱት አቶ ተስፋየ ፣ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አንቦ በሚገኘው ማዕረገ ሕይወት ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ትምህርት ቤት፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አዲስ አበባ በሚገኘው ጄኔራል ዊንጌት አዳሪ ት/ቤት ውስጥ ተከታትለዋል። ባሕርማዶ ሄደው የመማር እድል በማግኘታቸው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሊባኖስ ቤሩት በሚገኘው አሜሪካን ዩንቨርሲቲ ተምረዋል። ሁለተኛውን ዲግሪያቸውን ደግሞ በአሜሪካ ኒውዮርክ በሚገኘው ሲራከስ ዩኒቨርሲቲ በኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ ሳይንስ ዘርፍ በማእረግ ተመርቀዋል።
የኢትዮጵያን መንግስት በመወከል በጊዜው ደርግን ለመጣል ሲታገሉ ከነበሩት ሻእቢያ፣ ህወሃትና ኦነግ ጋር ለድርድር ወደ ሎንደን ሄደው የደርግ ስርዓት በመውደቁ እሳቸውም ለስደት ኑሮ ተዳርገዋል። አገር ወዳድ እና ለዘብተኛ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ተስፋዬ ዲንቃ በስደት ላይ እያሉ የዓለም ባንክን ጨምሮ በተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት ውስጥ እንዳገለገሉ ግለ ታሪካቸው ያስረዳል።
አቶ ተስፋዬ የአራት ልጆች አባት እና የአራት የልጅ ልጆች ዓያት ነበሩ።