ኢሳት (ኅዳር 30 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ምክንያት የከፋ የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸው ህጻናት ህይወት ለመታደግ አለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋማት የአምስት አመት ዘመቻን ጀመሩ።
በመንግስትና በ11 የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች የሚካሄደው ይኸው ዘመቻ 1.4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተመደበለት ሲሆን፣ ዘመቻው በከፋ የምግብ እጥረት ምክንያት የአካል መመናመን እየደረሰባቸው ያሉ ህጻናትና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ የሚረዳ መሆኑ ታውቋል።
በአማራ ክልል 46 በመቶ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 42 በመቶ እንዲሁም በአፋር 41 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት በከፋ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት የተነሳ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው እንደሚገኝ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ባለፈው አመት በሃገሪቱ የደረሰው የድርቅ አደጋ የተጎጂ ህጻናት ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽዖን ያደረገ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማም ተመሳሳይ የህጻናት የአካል መመናመን ችግር እንዳለ ተገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች ተከስቶ በነበረው የድርቅ አደጋ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸው ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የድርቁ አደጋ ዕልባት ባለማግኘቱ ምክንያት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ህጻናት አሁንም ድረስ የቅርብ ክትትል የሚፈልጉ ሆነው መቀጠላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል።
ከአንድ አመት በፊት ተከስቶ የነበረው የድርቅ አደጋ ዕልባት ባላገኘበት ወቅት አዲስ የድርቅ አደጋ በበርካታ የአርብቶ አደር አካባቢዎች መከሰቱ ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉን የተባበሩት መግስታት ድርጅት ይገልጻል።
በአሁኑ ወቅት 9.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ለምግብ ድጋፍ ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን፣ አዲስ የተከሰተው የድርቅ አደጋ የተረጂዎች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል ተብሎ ተሰግቷል።