በአፍሪካ የቀጭኔ ዝርያዎች እየተመናመኑ በመምጣት ላይ ናቸው ተባለ

ኅዳር ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በከፍተኛ ሁኔታ የሕዝብ ብዛት መጨመርን ተከትሎ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙ የቀጭኔ ዝርያዎች እየተመናመኑ መጣታቸውን ዓለምአቀፍ የተፈጥሮ ጥበቃ ኅብረት International Union for the Conservation of Nature (IUCN) አስታወቀ። ድርጅቱ በጥናታዊ ሪፖርቱ እንዳመላከተው በአፍሪካ ውስጥ በእ.ኤ.አ.1985 ቁጥራቸው 155 ሽህ የነበሩ የቀጭኔ ዝርያዎች እ.ኤ.አ በ2015 ዝርያቸው ተመናምኖ ወደ 97 ሽህ ዝቅ ብሏል።

ለቀጭኔ ዝርያዎች መመናመን ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተከትሎ የእንስሳቱ መኖሪያዎች ለሰዎች መኖሪያነት መዋል፤ ሕገወጥ አደን መስፋፋት፣ የእርስበርስ ጦርነቶች በጥናቱ በዋና ምክንያትነት ተጠቅሰዋል። በተወሰኑ የደቡባዊ አፍሪካ አገራት የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመሩ ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት መፍጠሩንም ዓለምአቀፍ የተፈጥሮ ጥበቃ ኅብረት አስታውቋል።

በሶስት ትውልድ ጊዜ ውስጥ 30% የሚሆኑ የቀጭኔ ዝርያዎች ጠፍተዋል። ይህን አስመልክቶ በድርጅቱ የቀጭኔ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር ጁሊያና ፌኔሲ እንዳሉት ”በየትኛውም ሳፋሪዎች ብትሄዱ ቀጭኔዎችን ታገኙዋቸው ነበር። አሁን ግን ልክ እንደ ዝሆን እና አውራሪስ ቀጭኔዎችም ሰለባ እየሆኑ ነው። ቀጭኔዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥራቸው እየተመናመነ ዝርያቸው እየጠፋ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ የዝምታ ጥፋት ልንታደጋቸው ይገባል” ብለዋል።

ዶ/ር ጁሊያና ፌኔሲ አክለው ”በተለይ የጦርነት ቀጠና የሆኑት በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ፣ በሰሜናዊ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ሁኔታዎች ይበልጥ የከፉ ናቸው። በአንጻሩ በደቡብ አፍሪካ ባለፉት ሃያና  ሰላሳ ዓመታት ውስጥ በሁለት እና ሶስት እጥፍ ቁጥራቸው ጭማሪ አሳይቷል። ወደ ምስራቅ አፍሪካ አገራት ስትመጣጡ ግን ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ በተለይ የኑቢያን ቀጭኔ ዝርያዎች ቁርጥራቸው እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ከ95% ከመቶ በላይ ተመናምነዋል” ብለዋል።

የተለያዩ የዱር እንስሳት እና አእዋፍት ዝርያቸው ተመናምኖ እንዳይጠፋ የአፍሪካ አገራት የደቡብ አፍሪካን ተሞክሮ በዓርአያነት በመውሰድ ሊታደጓቸው ይገባል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።