የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅም ማስተካከያ እንዲደረግበት የአለም ባንክ ጠየቀ

ኢሳት (ኅዳር 28 ፥ 2009)

የአለም ባንክ ኢትዮጵያ አጋጥሟት ያለውን የውጭ ንግድ ገቢ ለማነቃቃት የሃገሪቱ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ብር ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅም ማስተካከያ እንዲደረግበት አሳሰበ።

ባንኩ ከአምስት አመት በፊት ያቀረበውን ተመሳሳይ ሃሳብ ተከትሎ ብር ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅም በ15 በመቶ አካባቢ እንዲቀንስ መደረጉ ይታወሳል።

ከአምስት አመት በፊት ሁለተኛ ዙር ማስተካከያ በብር ላይ እንዲደረገ ያሳሰበው የአለም ባንክ እየተዳከመ የመጣውን የውጭ ንግድ ገቢ ሊያግዝ እንደሚችል አመልክቷል።

የብሄራዊ ባንክ በበኩሉ ከባንኩ የቀረበው ሃሳብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል በማለት እንዳማይቀበለው የገለጸ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ዕርምጃ በተወሰደ ጊዜ በሃገሪቱ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መከሰቱን በማስረጃነት አቅርቧል።

የብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዢ የሆኑት አቶ ዮሃንስ አያሌው የምንዛሪ ማሻሻያ እንዲደረግ የቀረበው ሃሳብ ሊያመጣው ከሚችለው ጥቅም በላይ ጉዳቱ ሊያይል ይችላል ሲሉ ለሃገር ውስጥ መገኛኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ሪፖርቱን ያቀረበው የአለም ባንክ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ካለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ወዲህ ከፍተኛ መዋዠቅ ማስመዝገቡን ይፋ አድርጓል።

ሃገሪቱ አጋጥሟት ያለው የውጭ ንግድ ገቢ መቀነስ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ላይ እያስከተለ ካለው ጉዳት በተጨማሪ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መስቀለኛ መንገድ ውስጥ እንደከተተው ባንኩ በሪፖርቱ አስፍሯል።

ኢትዮጵያ አጋጥሟት ያለውን ዘርፍ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት የብር የመግዛት አቅምን መቀነስ እንዲሁም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረጉ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ባንኩ አጽንዖት ሰጥቷል።

ይሁንና የአለም ባንክ ብር ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅም መቀነስ እንዳለበት ቢያሳስብም የሃገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ በምን ያህል መጠን ማሻሻያ እንዲደረግበት ያስቀመጠው አህዝ የለም።

በብሄራዊ ባንክ የረቡዕ መረጃ መሰረት አንድ የኢትዮጵያ ብር 22 ብር ከ 30 ሳንቲም በመመንዘር ላይ ሲሆን፣ በጥቁር ገበያ ደግሞ አንድ ዶላር ከ25 ብር በላይ በመሸጥ ላይ መሆኑን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ሃገሪቱ አጋጥሟት ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች በስራቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ይገልጻሉ።