ኢሳት (ኅዳር 28 ፥ 2009)
በአፍሪካ አሳሳቢ እየሆኑ በመጡ የሰብዓዊ መብት እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ዙሪያ የአህጉሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች በአዲስ አበባ ሊሰባሰቡ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ረቡዕ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ውጥረት ተደጋጋሚ መግለጫን ሲያወጣ የቆየው ህብረቱ አባል ሃገራቱ በአፍሪካ የሰብዓዊ መብት የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ዙሪያ ለሁለት ቀን እንደሚመክሩ ገልጿል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ተደርጎበት በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ሃሙስና አርብ የሚሰባሰቡት የአህጉሪቱ 54 አባል ሃገራት ተውካዮች በጸጥታና በደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በሰፊው እንደሚመክሩ ታውቋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ህብረት ያልተለመደ ነው በተባለው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ለህዝባዊ ተቃውሞ ሰላማዊ መፍትሄን እንዲሻ ጥያቄ ማቅረቡ ያታወሳል።
ለተከታታይ ሁለት ቀናት በመዲናይቱ አዲስ አበባ የሚካሄደው ይኸው አህጉራዊ ልዩ ጉባዔ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአባል ሃገራት ያሉ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን ይመረምራል ተብሎ ይጠበቃል።
ይኸው የኮሚሽኑ ልዩ ጉባዔ በአፍሪካ ከምርጫ ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ተያያዥ ጉዳዮች አንስቶ የሚወያይ ሲሆን፣ በቅርቡ በሶማሊያ ሊካሄድ በታቀደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ ይመክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
ለቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት የሚወዳደሩት አምስት የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት በዚሁ ጉባዔ እቅዳቸውን ያስተዋውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለህብረቱ ስድስት የኮሚሽን ቦታን ጨምሮ ቀጣዩ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ለሚሆኑ 41 ተወካዮች በእጩነት ቀርበው የሚገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለአንድ የኮሚሽን ቦታ ያቀረበችውን እጩ ከውድድር ውጭ ማድረጓ የሚታወስ ነው።
በርካታ የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የህብረቱ አባል ሃገራት ለሁለት ቀን የሚያካሄዱት የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት መድረክ አበይት ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት ውሳኔን እንደሚያስተላለፍ ጥሪን በማቅረብ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አባል ሃገራቱን በማሰባሰብ እንዲህ ያለ ጉባዔን በአዲስ አበባ ሲያክሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።