ኢሳት (ኅዳር 28 ፥ 2009)
በቅርቡ በጋምቢያ በተካሄደ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በተቃዋሚ ፓርት እጩ የተሸነፉት የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ክስ ሊመሰርትባቸው መሆኑ ተገለጸ።
ከ20 አመት በላይ በስልጣን ቆይተው የነበሩት ተሸናፊው ፕሬዚደንት ያ’ህያ ጃምህ በስልጣን ጊዜያቸው የሰብዓዊ መብት ረገጣን ሲፈጽሙ እንደነበር በተለያዩ አካላት ሲገለጽ ቆይቷል።
አዲሱ የጋምቢያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት ፕሬዚደንቱ በፈጸማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊከሰሱ በመሆኑ ከጋምቢያ እንዳይወጡ ትዕዛዝ መተላለፉን ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ሽንፈታቸውን የተቀበሉት ተሰናባቹ ፕሬዚደንት ወደ ትውልድ መንደራቸው ለመሄድ ጥያቄን ቢያቀቡም በሃገሪቱ ባለስልጣናት እቅስቃሴን እንዳያደርጉ እገዳ እንደተጣለባቸው ዘጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል።
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት አመራር የሆኑት ፋቱማታ ጃሎ ፕሬዚደንት ያህያ ክሳቸው የሚታየው በጋምቢያ ይሁን በአለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት እስካሁን ድረስ የተወሰነ ነገር አለመኖሩን ገልጸዋል።
ተሸናፊው ፕሬዚደንት ወደ ትውልድ ስፍራቸው ለመሄድ ያቀረቡት ጥያቄ ምናልባት በደጋፊዎቻቸው የደፈጣ ውጊያን ሊያካሄዱ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬን በማሳደሩ ምክንያት እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ እንደተጣለባቸው ታውቋል።
በመፈንቅለ መንግስት ለስልጣን የበቁት ተሰናባቹ ፕሬዝደንት በ22 አመት የስልጣን ዘመናቸው በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ጋዜጠኞች እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች እንዲታሰሩ ማድረጋቸው ይነገራል።
የተቃዋሚ ፓርቲ ስልጣን መያዙን ተከትሎ በህይወት ያሉ እስረኞች በመለቀቅ ላይ ሲሆኑ፣ ፕሬዚደንት ያህያ በቅርቡ ለእስር ይበቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ተሸናፊው የጋምቢያ ፕሬዚደንት ያህ’ያ ከአዲሱ የጋምቢያ ፕሬዚደንት አዳማ ባሮው ጋር በአካል በመገኛኘት ጥያቄን ቢያቀርቡም የተቃዋሚ ፓርቲ ጥምረት ጥያቄውን እንዳልተቀበለው የፓርቲው አመራሮች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የፕሬዚደንት ጃሜህ ባለቤት በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች የሚጠረጠሩ በመሆኑ የተናጠል ክስ ሊመሰረትባቸው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። ከቀድሞው የሊቢያ ፕሬዚደንት ሞሃመድ ጋዳፊ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው የጋሚቢያው ፕሬዚደንት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በስማቸው ሊኖር እንደሚችል መጠርጠሩንና ጋምቢያ ጉዳዩን ለመመርመር ብሄራዊ ኮሚሽን ማቋቋሙን ዘጋርዲያን ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።
ፕሬዚደንት ያህያ መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ወደ ሌላ የአፍሪካ አባል ሃገር እንዲዛወር ከጥቂት አመታት በፊት ከቀድሞው የሊቢያ ፕሬዚደንት ሞሃመድ ጋዳፊ ጋር ቅስቀሳን ሲያካሄድ እንደነበር ይታወሳል።