ኢሳት (ኅዳር 27 ፥ 2009)
የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ገቢ ንግድ ከወጪ ንግድ ገቢ ያለው ልዩነት እየጨመረ መምጣቱንና ከ10 በመቶ በላይ መድረሱን ማክሰኞ ይፋ አደረገ።
በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዙሪያ አምስተኛ ሪፖርትን ያወጣው ባንኩ የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ አለመመጣጠን በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጿል።
የኢትዮጵያ የስራ አጥ ችግርም ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ሲነጻጸት በመጠን ከፍተኛ መሆኑን የባንኩ ሪፖርት አመልክቷል።
ባለፉት ጥቂት አመታት መታየት የጀመረው የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ገቢ መቀነስ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ያስታወቀው የአለም ባንክ ሃገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ መሆኗንም አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የተከሰተው የድርቅ አድጋ በኦሮሚያ ክልል ለአንድ አመት ያህል ጊዜ ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ በሃገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩንም የባንኩ ሪፖርት ይገልጻል።
ሃገሪቱ አሁን አጋጥሟት ያለውን ሁለገብ ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ከማሳደግ በተጨማሪ የስራ አጥነት ችግርን መቅረፍ እንዲሁም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የአለም ባንክ የመፍትሄ ሃሳብ ብሎ ለመንግስት ካቀረባቸው ነጥቦች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
መንግስት የ2015/2016 አም የኢክኖሚ ዕድገቱ በሁለት አህዝ ያድጋል ብሎ የነበረ ቢሆንም የአለም ባንክ ዕድገቱ በስምንት በመቶ አካባቢ መመዝገቡን አክሎ አስፍሯል።
በኢትዮጵያ ያለው የስራ አጥነት ችግር በኢኮኖሚ ዕድገቱ ሊፈታ አለመቻሉን ያወሳው ባንኩ ከ20 በመቶ በላይ ላይ የሚገኘው የስራ አጥ አህዝ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳና ሌሎች የአህጉሪቱ ሃገራት የስራ አጥ ቁጥራቸው ከ10 በመቶ በታች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዘፍሩ ያለባትን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባት ባንኩ አክሎ አሳስቧል።
የአለም ባንክና ሌሎች የፋይናንስት ተቋማት ከ36 ቢሊዮን ዶላር በላይ የደረሰው የሃገሪቱ የእዳ ክምችት ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን ሲፈታተን መቆየቱን ሲገልጹ ቆይተዋል።
በውጭ ብድር በመካሄድ ላይ ያሉ የልማት ፕሮጄክቶች በታቀደው መሰረት ተግባራዊ ሊሆኑ ካልቻሉ በቀጣዩ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተጨማሪ ተፅዕኖን ሊያሳድሩ ይችላሉ ሲሉ በባንኩ የአፍሪካ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ፓሎማ ካሴሮ ገልጸዋል።