የወልድያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ታሰሩ

ኅዳር ፳፮ (ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 24 ቀን 2009 ዓም በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ የብሄር ብሄረሰቦችን በአል ለማክበር በተጠራ ዝግጅት ላይ “ተማሪዎች በአሉ እኛን አይወክልም” በማለት ከመሰብሰቢያ አዳራሹ በመውጣት በጩኸት ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ የፌደራል ፖሊሶች ወደ ዩኒቨርስቲ ግቢ በመግባት 37 ተማሪዎችን ይዘው አስረዋል።

የአማራ ክልል ተወላጆች “ ወልቃይት ማንነቱ አማራ ነው” የሚሉና ሌሎችንም አገዛዙን የሚያወግዙ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን፣ የዩኒቨርስቲው ባለስልጣናት ፖሊሶች እርምጃ እንዲወስዱ ፈቃዳቸውን ሰጥተው ተማሪዎች እንዲያዙ አድርገዋል።

በአሁኑ ሰአት በእስር ላይ የሚገኙ የ37 ተማሪዎች ስም ዝርዝር የደረሰን ቢሆንም፣ የዩኒቨርስቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ኪዳኔ ማርያም ግን በእስር ላይ የሚገኙት ተማሪዎች ቁጥር ከ11 አይበልጥም በማለት ለኢሳት ተናግረዋል። ተማሪዎቹ የተያዙት ከተፈቀደው መፈክር ውጭ የራሳቸውን መፈክሮች በጩኸት በማሰማታቸው ነው ብለዋል።