“ለቁንጽል መፍትሄ ብለን ከዚህ መንግስት ጋር የሚያደራድረን የለም” ሲሉ ዶ/ር ዲማ ነገዎ ተናገሩ

ኅዳር ፳፮ (ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በቅርቡ በ4 የፖለቲካ ድርጅቶች የተመሰረተው የኢትዮጵያ አገራዊ  ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶ/ር ዲማ ነገዎ ይህን የተናገሩት፣ በጀርመን የሙኒክ ከተማ ንቅናቄውን ለህዝብ ለማስተዋወቅና ድጋፍ ለመሳበሰብ በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ነው። “ኢህአዴግ አርበኞች ግንቦት7 ትን ካወገዛችሁ ከእናንተ ጋር ድርድር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ቢላችሁ፣ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ዝግጁ ትሆናላችሁ? “ ወይ ተብሎ ለቀረቡላቸው ጥያቄ ፣ ዶ/ር ዲማ ሲመልሱ “ ወያኔ እናናግራችሁ ካለን የሚያናግረን 4ታችንም ነው፣ ለቁንጽል መፍትሄ ከዚህ መንግስት ጋር አንደራደርም” የሚል መልስ ሰጥተዋል።

በዚህ ስብሰባ ላይ ንግግራቸውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ የስራ አስፈጻሚ አባልና የአፋር ነጻ አውጭ  መሪ ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ ፣ የምንታገለው ጠላት አገሪቱን በጎሳ አደራጅቶ ህዝብን በተለያዩ መንገዶች በመፈረጅ እርስ በርስ በማጋጨት እንዲሁም ያለ የሌለ ጉልበቱን ተጠቅሞ በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚፍልግ በመሆኑ ተባብሮ በጋራ መታገልን አስፈልጊ አድርጎታል ብለዋል።

ዶ/ር ኮንቴ እስከዛሬ በርካታ ጥምረቶች መፈጠራቸውን አውስተው ይሁን እንጅ ይህን ጥምረት እስከዛሬ ከተደረጉት ጥምረቶች የሚለየው በመተማመን ላይ የተመሰረተ እና ለስልጣን ሳይሆን ህዝብን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ የተመሰረተ  በመሆኑ ነው ሲሉ አክለዋል።

የንቅናቄው ሊቀመንበር የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ከፍተኛ የአመራር አባል የሆኑት ዶ/ር ዲማም እንዲሁ የአዲሱን ንቅናቄ አስፈላጊነት በኦሮምኛና በአማርኛ አቅርበዋል። ዶ/ር ዲማ ፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ የተካሄደው ህዝባዊ ትግል መሪዎቹ ታስረውበት እንኳ ትግሉ መቀጠል መቻሉ አዎንታዊ ገጽታው ቢሆንም፣ ማእከላዊ አመራር የሌለው መሆኑ ሂደቱን እንደጎዳው ገልጸዋል። ይህንን የአመራር ክፍተት ለመሙላት አገራዊ ንቅናቄው መመስረቱን ዶ/ር ዲማ አስረድተዋል።

ለኢትዮጵያ ከእንግዲህ የሚያስፈልገው የመንግስት ለውጥ ሳይሆን የስርዓት ለውጥ ነው የሚሉት ዶ/ር ዲማ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ በሁዋላ የምትፈልገው ህዝብ ሲፈልግ መሪዎቹን ወደ ስልጣን የሚያወጣበትን ፣ ሳይፈልግ ደግሞ የሚያወርድበትን ስርዓት በመሆኑ፣ ሁላችንም ለዚህ ስርዓት መመስረት የበኩላችንን እንስራ ብለዋል።

ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው የአገራዊ ንቅናቄውን መመስረት ተከትሎ የሚነሱትን ጥያቄዎችና ብዥታዎች ለማጥራት የሞከሩት የአገራዊ ንቅናቄው ም/ል ሊቀመንበርና የአርበኞች ግንቦት7 መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ አገራዊ ንቅናቄው በሁለት አንኳር ጉዳዮች ላይ ስምምነት አድርጎ የተመሰረተ ነው ብለዋል። አንደኛው፣  ስምምነቱን የፈረሙት አራቱም ድርጅቶች የኢትዮጵያን ሉአላዊ አንድነት የሚቀበሉ መሆናቸው ሲሆን ፣ ሌላው ደግሞ ሁሉም ድርጅቶች ከእንግዲህ የሚመሰረተው ስርዓት ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን መስማማታቸው ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አገራዊ ንቅናቄው ለህዝብ ይፋ በተደረገበት ወቅት የብሄር ውክልና ያለበት መስሎ እንዲቀርብ መደረጉ ስህተት ነበር ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ፣ ንቅናቄው የድርጅቶች እንጅ የብሄሮችን ውክልና መሰረት አድርጎ ያልተመሰረተ በመሆኑ፣ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት የኢትዮጵያን አንድነት የሚቀበል ከሆነና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ምስረታ ለመታገል ዝግጁ ከሆነ በጥምረቱ ውስጥ ገብቶ መሳተፍ እንደሚችል ተናግረዋል። በጥምረቱ ውስጥ የአማራ ህዝብ አልተወከለም በሚል የሚቀርበው ትችት ተገቢ የማይሆነው፣ ጥምረቱን የመሰረቱት ሃይሎች በብሄር ደረጃ እንደራደር ብለው ያልቀረቡ መሆናቸውና በብሄር ውክልና ድርድር ለማድረግ ፍላጎቱም እቅዱም የሌለ በመሆኑ ነው ሲሉ ያብራሩት ፕ/ር ብርሃኑ፣ ሆኖም በአማራው ስምም ይሁን በየትኛውም ብሄር ተሰባስበው የሚመጡ ሃይሎች በቅድመ ሁኔታ የተቀመጡትን ሁለቱን መስፈርቶች እስካሟሉ ድረስ ተጣምረው ለመስራት የሚከለክላቸው ነገር የለም።

በስብሰባው የተሳተፉት በርካታ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ ለጥያቄዎቹ መሪዎች መልስ ሰጥተዋል። ዝግጅቱን የሙኒክ የአርበኞች ግንቦት7 የስራ አስፈጻሚ አባላት ያዘጋጁት ሲሆን፣ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ስነስርዓት ላይ በተደረገ ጫረታ የነጻነት ትግሉን በገንዘብ እና በተለያዩ መንገዶች በመደገፍ የሚታወቁት ዶ/ር ጌታነህ ቡሊ ፣ በቢሾፍቱ ኢሬቻ በአል ላይ በተፈጸመው እልቂት ወቅት ወያኔ ይወደም  በእንግሊዝኛ “ዳውን ዳውን ወያኔ” በማለት መፈክር ሲያሰማ ለነበረውና በአሁኑ ሰአት በስደት ላይ በሚገኘው ገመዳ ዋሪዮ ስም ተወዳድረው ከ14 ሺ ዩሮ በላይ በሆነ ዋጋ የአቶ በቀለ ገርባ፣ አንዳርጋቸው ጽጌና ኮ/ል ደመቀ ዘውዴን ምስል የያዘውን ሽልማት አሸንፈው ወስደዋል።

በጨረታው ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ላሸነፉት ተወዳዳሪዎች ደግሞ አትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ ያበረከተውን ቲሽተርት እና ዋንጫ ተሸልመዋል።