የፌደራል ፖሊሶችና ወታደሮች ሃረርን አጨናንቀዋል

ኅዳር ፳፮ (ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ወኪላችን እንደገለጸው ህዳር 29 የሚከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች በአል ምክንያት በማድረግ በከተማው የሚታየው የጸጥታ ቁጥጥር የከፋ መሆኑን ገልጿል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች ወደከተማ የገቡ ሲሆን፣ ለጸጥታ ስጋት ናቸው የተባሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተይዘው ታስረዋል።

ከሃረር ወጣ ብሎ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች በርካታ የኦሮሞ ወጣቶች ተይዘው ታስረዋል። ከ500 በላይ የሚሆኑ የአማራ እና የሌሎችም አካባቢ ተወላጆች ከተለያዩ አካባቢዎች ተይዘው  በምስራቅ እዝ ወታደራዊ ግቢ ውስጥ መታሰራቸውንም ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ወኪላችን ዘግቧል። የባጃጅ አሽከርካሪዎች በአሉ እስከሚጠናቀቅበት ሰአት ድረስ በዋና ዋና መስመሮች እንዳይሰሩ ታግዷል። ትምህርት ቤቶች ለእንግዶች ማረፊያ በሚል ተዘግተዋል።

ነጋዴዎች ደግሞ ከመዘጋጃ ቤት ከ70 እስከ 100 ብር በሚደርስ ዋጋ የክልሉን ባንዲራና ባለኮከቡን የአገሪቱን ባንዲራ ገዝተው በድርጅቶቻቸው ላይ እንዲሰቅሉ ታዘዋል።

በአሉ በ 1 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ በአፍረጺዮን ኮንስትራክሽን በተገነባው ስታዲየም የሚከበር ሲሆን፣ ከተማዋን የማስዋብና ሌሎችንም ተጓዳኝ ሰራዎች ከህወሃት ጋር በቅርበት የሚሰሩ ድርጅቶች ኮንትራት ወስደው እየሰሩ ነው።