ኢሳት (ኅዳር 26 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ በተከሰተው አዲስ የድርቅ አደጋ አምስት አካባቢዎች አስቸኳይ ርብርብ የሚፈልጉ ሆነው መለየታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰኞ ይፋ አደረገ።
በርካታ እንስሳት በድርቁ ምክንያት በመሞት ላይ መሆናቸውን የገለጸው ድርጅቱ የደቡብ ኦሮሚያ፣ በደቡብ ኦሞ የሰገን እና ጋሞጎፋ አጎራባች ስፍራዎች እንዲሁም የሶማሊ ክልል አዲስ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ቅድሚያ ተኮር ተደርገው አስቸኳይ ርብርብ የሚፈልጉ ተብለው መፈረጃቸውን አመልክቷል።
በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በመስፋፋት ላይ በመሆኑ በቀጣዮቹ ስድስት ወራቶች የምስራቅ ኦሮሚያ እንዲሁም በደቡብ ክልል የሚገኙ በርካታ ዞኖች በአንደኛ ደረጃ የድርቅ አደጋ ውስጥ ሊካተቱ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅቱ አሳስቧል።
በመሞት ላይ ያሉ የቤት እንሳሳትን ለመታደግ ብቻ 27 ሚሊዮን ዶላር (ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ) እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች በድርቁ ጉዳት የሚያስፈልገውን ድጋፍ በመመርመር ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ከአንድ አመት በፊት በስድስት ክልሎች ተከስቶ የነበረው የድርቅ አደጋ ዕልባት ሳያገኝ አዲስ የድርቅ አደጋ መከሰቱን ችግሩን ያባብሰዋል ተብሎ ተሰግቷል።
በአሁኑ ወቅት 9.7 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለምግብ ድጋፍ ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን ይህ ቁጥር በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪን ሊያሳይ እንደሚችል አለም አቀፉ የእርዳታ ተቋማት በማሳሰብ ላይ ናቸው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ “የድርቁ አደጋ ከእጃችን ሳይወጣ ያለንን ልምድ ተጠቅመን በቁጥጥር ስር እናውለዋለን” ሲሉ አዲስ የተከሰተውን የድርቅ አደጋ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት በበኩላቸው ተጨማሪ ጊዜ ሳይወስድ አስቸኳይ የእርዳታ ድጋፍ ስራ መከናወን እንዳለበት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።