ኢሳት (ኅዳር 26 ፥ 2009)
ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ የሚገኙ የሃገሪቱ የተቃዋሚ ድርጅቶች ጽ/ቤት እንዲዘጉ ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ገለጹ።
ሰሞኑን ሚስጢራዊ የጦር መሳርያ ግዥን ለመፈጸም የተስማሙት ሁለቱ ሃገራት በሪክ ማቻር የሚመራው የሱዳን ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ በኢትዮጵያ ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ እንዲያበቃ ድርድር ሲያካሄዱ መቆየታቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ዘግቧል።
በሁለቱ ሃገራት መካከል የተደረሰን ስምምነት ተከትሎ መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ያደረጉ የአማጺያን ቡድን አባላት በአማጺ ቡድኑ ወደተያዙ የደቡብ ሱዳን ግዛቶች ሊሄዱ እንደሚችሉ አሊያም በኢትዮጵያ የጥገኝነት ጥያቄን ሊያቀርቡ እንደሚችሉ የፖለቲካ ተንታኞች አስታውቀዋል።
የአማጺ ቡድኑ መሪ ሪክ ማቻር ከአንድ አመት በላይ በኢትዮጵያ መንግስት የማረፊያና ሌሎች አገልግሎቶች ቀርቦላቸው ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ድርድር ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይሁንና ማቻር ስምምነት ከደረሱ በኋላ ለተግባራዊነቱ ቁርጠኝነትን አላሳዩም በማለት አሜሪካና የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በማቻር ላይ ቅሬታን ሲያቀርቡ ሰንብተዋል።
በሪክ ማቻር ላይ መቅረብ የጀመረውን ቅሬታ ተከትሎም ኢትዮጵያ የአማጺ ቡድኑ መሪ ወደ ሃገሯ ተመልሰው እንዳይገቡ እገዳን የጣለችው ሲሆን የማቻር አማጺ ቡድን ኢትዮጵያ የወሰደችን ውሳኔ ማውገዙ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ማቻር ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ ከጣለው እገዳ በተጨማሪ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የአማጺ ቡድን አመራሮች ቢሮአቸውን እንዲዘጋ የቀረበለትን ጥያቄ መቀበሉንም የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ለሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ አስታውቀዋል።
ይሁንና ጽ/ቤቱ መቼ እንደሚዘጋና ምን ያህል የቡድኑ አመራሮችና አባላት በኢትዮጵያ እንደሚገኙ የተገለጸ ነገር የሌለ ሲሆን፣ የሪክ ማቻር አማጺ ቡድን በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታን እያቀረበ ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ግምት ያለው የጦር መሳሪያ ግዥን ለማካሄድ ስምምነት እንደደረሱ በደቡብ ሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘንድ ይፋ ተደርጓል።
በጉዳዩ ዙሪያ ሁለቱ ሃገራት እስካሁን ድረስ የሰጡት ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ የሌለ ሲሆን፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት በሪክ ማቻር አማጺ ቡድን ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የደቡብ ሱዳን መንግስት ተወካዮችና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት ሪክ ማቻር ዕሁድ በአካል አገናኝቶ ለማደራደር የተደረገ ጥሪ አለመሳካቱን ለመረዳት ተችሏል።