ኅዳር ፳፫ (ሃያ ሦስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር እና የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና እስራት እንዳሳሰበው የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በቃል አቀባዩ በኩል የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
በአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ምክትል ቃል አቀባይ የሆኑት ማርክ ቶነር እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት ዶ/ር መረራ ጉዲና ማሰሩን የአሜሪካ መንግስት መንግስት እያሳሰበው መምጣቱን እና ሁኔታዎችንም በቅርበት መንግስታቸው እየተከታተለ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ዶ/ር መረራ ጉዲናን ማሰሩ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ውስጥ የነጻነት ድምጾችን ለማፈን በዜጎች ላይ የሚጣሉት ገደቦች እየተጠናከሩ መምጣታቸውን ማሳያ ነው።
በአገሪቱ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡትን ሕጋዊ መብቶችን ለማፈኛነት መንግስት እየተጠቀመበት መሆኑን ያመላክታል። የኢትዮጵያ መንግስት ለተፈጠሩት አገራዊ ችግሮች ፖለቲካዊ ለውጦችን አመጣለሁ ካለው ውሳኔ ጋር ተጻራሪ የሆነ ድርጊት መሆኑን እና ሁኔታዎች በቅርበት መንግስታቸው እንደሚከታተለው ቃል አቀባዩ ማርክ ቶነር አሳስበዋል።