ነዋሪነቱ በአውስትራሊያ ሜልቦርን ከተማ ውስጥ የሆነ የሰላማዊ ሰልፈኛ ቤተሰብ ታሰሩ ።  

ኅዳር ፳፫ (ሃያ ሦስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የቀድሞው የሕግ ጠበቃና ዳኛ የነበሩት ሽኩሪ ሻፊ በአውስትራሊያ ከሚገኙ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የሶማሌ ብሔር ተወላጆች ጋር በመኾን ባለፈው ግንቦት ወር ላይ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሃመድ ኡመር የሚያደርጉትን ጉብኝት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ነበር። አቶ ሽኩሪ ሻፊ በሜልቦርን ከተማ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፉ ላይ መሳተፋቸውን ተከትሎ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ሦስት ወንድሞቻቸውን ጨምሮ ወላጅ እናታቸው እና አንድ እህታቸው በኢትዮጵያ መንግስት ታስረዋል።

አቶ ሻፊ ስለተሰወሩት ሦስት ወንድሞቻቸው አስመልክቶ ሰሞኑን አንድ ዜና መሰማቱን ሲናገር “ወንድሞቼ መፈታታቸውን አውቄያለሁ” ይኹንና ላለፉት ሰድስት ወራት የት እንደነበሩ አድራሻቸው ያልታወቁት ወንድሞቹ ገርጥተው፣ ከስተውና በረሃብ ተጎሳቆለው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን አውስተዋል። “ወንድሞቼ ከስድስት ወራት በፊት ሲታሰሩ ለብሰውት የነብሩትን አልባሳት ለብሰው እላያቸው ላይ ነትቦ ነው ከእስር የተለቀቁት” የወንድሞቹን መለቀቅ እንደ መልካም ዜና የወሰደው አቶ ሽኩሪ ሌላ አሳዛኝ ዜና መስማቱንም ተናግዋል። “ለአንድ ወር ታስራ የተለቀቀችው እህቴ፤ አሁን በድጋሚ ከባለቤቷ ጋራ ወደ እስር ቤት መላኳን አውቂያለሁ” አቶ ሻፊ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ወቅት ለተከታታይ 16 ወራት ታስሮ ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ከፍተኛ እስርና ድብደባ ተፈጽሞበት እንደነበርም አቶ ሽኩሪ አውስቷል። ዓለም አቀፍ የስብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በግንቦት ወር በሜልቦርን ከተደረገው ተቃውሞ ጋራ በተያያዘ ቁጥራቸው ከ32 በላይ የሚሆኑ የተቃዋሚ ሰልፈኞች ዘመዶች ለእስራት መዳረጋቸውን ገልፀዋል።

“የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላማዊ ሰልፈኞቹን ቤተሰቦችና ዘመዶች በፍጥነት እንዲፈታና እንዲለቅ የውጪ መንግሥታት ከፈተኛ የኾነ ጫና ማሳደር ይኖርባቸዋል ሲሉ በሂውማን ራይትስ ዎች የአውትራሊያ ዳሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ኢላይነ ፔርሰን አሳስበዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ በኤንባሲው በኩል በሰጠው መግለጫ በተቃውሞ ሰልፍ ሰበብ የታሰሩ ዜጎች አለመኖራቸውን ማስተባበያ ሰጥቷል። የኢምባሲው የመረጃ ሠራተኛ የሆኑት አቶ ጀማል ሰይድ “የአቶ ሽኩሪ ሻፊ እህት አልታሰረችም፤ ከቤቷ ትገኛለች” ብለዋል።

ለቤተሰቦቹ ደኅንነት ሲል በሦስተኛ አገር በኩል መረጃ የሚለዋወጠው አቶ ሽኩሪ ሻፊ “መረጃው የተረጋገጠ ነው፤ በኢትዮጵያ መንግሥት ክህደት እኔ አልገረምም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። የአውስትራሊያ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሃመድ ጉብኝት ጋራ በተያያዘ ለእስር ተዳርገዋል የተባሉትን የሰላማዊ ሰልፈኛ ቤተሰቦችና ዘመዶች ጉዳይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ በጀመረው ምክክር እንደሚቀጥልበት ለሌትላይን ጠቅሶ ኤቢሲ ዘግቧል።