ኢሳት (ኅዳር 22 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ መንግስት ዶ/ር መረራ ጉዲናን ለእስር መዳረጉን በሃገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ውጥረት ወደ አለመረጋጋት ሊወስደው እንደሚችል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሃሙስ ገለጸ።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የተካሄደ አፈና ነው ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የምስራቅ አፍሪካ ምክትል ሃላፊ የሆኑት ሚቼሌ ካጋሪ አስታውቀዋል።
መንግስት የወሰደው ዕርምጃም በሃገሪቱ ያለውን ውጥረት እንደሚያባብሰው ያሳሰቡት ተወካዮዋ እርምጃው በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለሚከታተሉ አለም አቀፍ አካላት ጥሪን ያስተጋባ ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለአንድ አመት ያህል ጊዜ በኦሮሚያ ክልል በዘለቀውና በቅርቡ ወደ አማራ ክልል ከተዛመተው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ከ700 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ሲያሳውቅ ቆይቷል።
በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በሃገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ትርጉም ባለው መልኩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አክሎ አሳስቧል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና ለእስር በተዳረጉበት እለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊነት የሚከታተለው የኮማንድ ፖስቱ ሃላፊ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ አዋጁ በሃገሪቱ ላሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ሲሉ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
የሂውማን ራይትስ ዎች ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆንር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጥያቄ እያነሱ ካሉ አካላት ጋር ውይይት ይካሄዳል ሲሉ ቢገልጹም እያካሄዱት ያለው ነገር የተቃረነ ነው በማለት ለዋሽንግተ ፖስት ጋዜጣ አስረድተዋል።