ኢሳት (ኅዳር 22 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ መንግስት ለጎረቤት ደቡብ ሱዳን የተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በሽያጭ በማቅረብ ላይ መሆኑን የሃገሪቱ አንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም በብቸኝነት አግንቼዋለሁ ያለውን ሚስጢራዊ መረጃ ዋቢ በማድረግ አጋለጠ።
መቀመጫውን በአዲስ አበባ ባደረገው የደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ምክትል ወታደራዊ ተወካይ የሆኑት ሌተናል ኮሎኔል ሰለሞን ቶር ካንግ በሃገራቸው የመከላከያ ሚኒስትር አዛዥ ፓል ዋሎንግ አዋንግ የጦር መሳሪያዎቹን ወደ ጁባ እንዲጓጓዙ የ55ሺ ዶላር ክፍያን እንዲፈጽሙ የጠየቁበትን ደብዳቤ ኒያሚሌፒዲያ የተሰኘው የዜና አውታር መመልከት እንደቻለ ዘግቧል።
በሁለቱ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት መካከል የደብዳቤ ልውውጡ ባለፈው ሳምንት (እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ህዳር 25 ፥ 2016 አም ) መካሄዱን ያመለከተው የዜና አውታሩ የጦር መሳሪያዎቹ ደብረ ዘይት ከተማ ከሚገኝ የአየር ሃይል ማዘዣ ጣቢያ እንደሚጓጓዙ በደብዳቤው መስፈሩን አስነብቧል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ክፍያው እንዲፈጸምለት በጠየቀው ደብዳቤ የጦር መሳሪያዎቹን ከኢትዮጵያ እስከ ጁባ ከተማ ድረስ ሁሉንም ወጪ የሚሸፍን ይሆናል ሲል በሌላ ደብዳቤ ለደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ማድረሱንም ለመረዳት ተችሏል።
ወደ ደቡብ ሱዳን ይጓጓዛሉ ተብለው ከሚጠበቁት ከባድ የጦር መሳሪያዎች መካከል ባለ 107 ሚሊሜትር 20ሺ ሮኬቶች፣ ባለ 60 ሚሊ ሜትር ወደ 8ሺ የሚጠጉ ሞርታሮች 20ሺ RGD-5 የተሰኙ የእጅ ቦምቦች እንደሚገኙበት በሚስጢራዊ መረጃው በዝርዝር መቀመጡን የዜና ተቋሙ ዘግቧል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት የጦር መሳሪያዎቹን ከኢትዮጵያ ለመግዛት የወሰነው በአማጺ ቡድኑ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማካሄድ እንደሆነም ተመልክቷል።
የደቡብ ሱዳን መንግስትና በሪክ ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን የጋራ ብሄራዊ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ከተስማሙ በኋላ ዳግም ወደ ግጭት መግባታቸው ይታወሳል።
ከወራት በፊት በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰውን ይህንኑ ግጭት ተከትሎ ሪክ ማቻር በስደት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የአማጺ ቡድኑ ሃላፊ ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ እገዳን ጥላ ትገኛለች።
ማቻር ከአንድ አመት በላይ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ አድርገው ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ድርድር ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይሁንና ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ደርሰውታል የተባለን ስምምነት ተከትሎ ኢትዮጵያ ማቻር ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ ያደረገች ሲሆን፣ በቅርቡ አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ደርሰው የነበሩት ማቻር ወደ መነሻ ስፍራቸው ደቡብ አፍሪካ እንዲመለሱ መደረጉን መዘገባችን የሚታወቅ ነው።
በቅርቡ በደቡብ ሱዳን ጉብኝትን ያደረጉ የተባበሩት መንግስታት የዘር ማጥፋት ድርጊቶች አማካሪ አዳማ ዴንግ የጸጥታው ምክር ቤት በሃገሪቱ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ተግባራዊ እንዲያደርግ ጥሪን አቅርበዋል።
አሜሪካ በበኩሏ በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዳይሰፍን አስተዋጽዖን ባደረጉ አካላት ላይ የጉዞና የተለያዩ ማዕቀቦች እንዲጣሉ ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቧንም ለመረዳት ተችሏል።
የደቡብ ሱዳኑ የመገናኛ ተቋም የጦር መሳሪያውን ለማጓጓዝ በሚስጥራዊ መረጃው ከሰፈረው የገንዘብ መጠን በተጨማሪ ለመሳሪያው ግዢ ምን ያህል የገንዘብ ስምምንት እንደተደረገ የጠቀሰው ነገር የለም።
የኢትዮጵያም ሆነ የደቡብ ሱዳን መንግስታት በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡት ምላሽ አለመኖሩንም ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።