ኅዳር ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበርና የመድረክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና በአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በተጋባዥነት እንግድነት ንግግር አድርገው ወደ አገራቸው ሲመለሱ በህወሃት ኢህአዴግ ኮማንድ ፖስት በቁጥጥር ስር ውለዋል። የዶ/ር መረራ ጉዲናን መታሰር አስመልክቶ አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ አውጥቷል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ እና ታላላቅ ሃይቆች ምክትል ዳሬክተር የሆኑት ሚካኤል ካጋሪ እንዳሉት ”የዶ/ር መረራ ጉዲና እስራት የሚያመላክተው ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ መጠነሰፊ የሆነ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች በገሃድ መጨፍለቃቸውን ነው።
“ከዓመት በላይ የዘለቀው ሕዝባዊ እንቢተኝነቱ ላይ ያነጣረ የአደጋ ጊዜ ደውል ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ሕዝባዊ ቁጣዎች መልካቸውን ቀይረው አገራዊ ቀውሱ ተባብሶ ከመቀጠሉ አስቀድሞ አፋጣኝ እና ትርጉም ያላቸውን ማስተካከያዎችን ሊወስድ ይገባል” ሲሉ አክለዋል።
የዶክተር መረራ ጉዲናን እስራት አስመልክቶ ታላላቅ ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የሆኑት ቢቢሲ፣ ሮይተር፣ አልጀዚራና ዋሽንግተን ፖስትን የመሳሰሉት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በከፋ ሁኔታ ተባብሰው መቀጠላቸውን አጽንኖት ሰጥተው ዘግበዋል።
የገዥው ፓርቲ ህወሃት ልሳን የሆነው ፋና በበኩሉ ሰሞኑን ዶክተር መረራ ጉዲና በቤልጅየም ብራሰልስ በአሸባሪነት ከተፈረጀው ግንቦት ሰባት ቡድን መሪ ከሆኑት ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውንና መግለጫ መስጠታቸውን ለመታሰራቸው ምክንያት መሆኑን ዘግቧል።