በፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ቦንብ ተገኝቷል በሚል ሰበብ በርካታ ፖሊሶች ታሰሩ

ኅዳር ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከሶስት ቀናት በፊት ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው በፌደራል ፖሊስ ዋናው ጽ/ቤት ወንጀል ምርመራ ክፍል ውስጥ ቦንብ ተገኝቷል በሚል ሰበብ በርካታ የኦሮሞና አማራ ተወላጅ ፖሊሶች ታሰረዋል።

ምንጮች እንደገለጹት ቦንቡ ሆን ተብሎ ፖሊሶችን ለማጥመድ ተብሎ በህወሃት የፌደራል ፖሊስ አባላትና የደህንነት ሰዎች የተቀነባባረ ነው። በወንጀል ምርምራ ክፍል ውስጥ የጦር መሳሪያ እንደማይገባ የሚገልጹት ምንጮች፣ ድርጊቱ አገዛዙን ይቃወማሉ ተብለው የሚታሰቡትን የሁለቱን ብሄር ተወላጅ ፖሊሶችን ለመወንጀል ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ይህንን ተከትሎ በእለቱ ተራኛ የነበሩ ዘበኞች ሳይቀሩ ታስረዋል።

ኢሳት የፌደራል ፖሊስ አባላት ውስጣዊ ተቃውሞ እያሰሙና ስራቸውንም እየለቀቁ መሆኑን ቀደም ብሎ መዘገቡ ይታወቃል። ነባር የኦሮሞና የአማራ ወንጀል ምርመራ ፖሊሶችን በማባረር በምትካቸው አዳዲስ አስልጠነው ያመጡዋቸውን ወጣት ምሩቃን እየቀጠሩ ነው።

በወንጀል ምርመራ ወቅት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ተከሳሾች ጉዳይ በአማራ ተወላጅ መርማሪዎች፣ የአማራ ተወላጅ ተከሳሾችን ጉዳይ በኦሮሞ ተወላጅ መርማሪዎች እንዲታይ በማድረግ የሁለቱ ብሄር ተወላጅ ፖሊሶች እና ዜጎች እርስ በርስ እንዲጋጩ ሙከራ ሲደረግ መቆየቱንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል።