በፍኖተሰላም በህገወጥ መንገድ የተገደሉ እስረኞችን ቀብር ያጋለጡ አባት ታሰሩ

ኅዳር ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በምዕራብ ጎጃም ዞን በፍኖሰላም ከተማ ተፈጥሮ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከታሰሩት መካከል የ2 እስረኞች አስከሬን በድብቅ በሌሊት በቁስቋም ቤተክርስቲያን ሲቀበር የተመለከቱት ሊቀ ጳጳስ መካነ ሰላም፣ ድርጊቱን በመቃወማቸውና ድርጊቱንም ለህዝብ በመንገራቸው መታሰራቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ሊቀ ጳጳሱ ለቁስቋም ቤተክርስቲያን ንግስ ከደብረሊባኖስ ገዳም ወደ ፍኖተሰላም መሄዳቸውን የገለጹት ምንጮች፣  በቅዳሴ ሰአት ፖሊሶች ሁለት ወጣቶችን ሲቀብሩ ተመልከተው፣ ድርጊቱ ህገወጥ መሆኑን ለፖሊሶች ነግረዋቸዋል። በእለቱ በነበረው የስብከት ስነስረዓት ላይም ድርጊቱን ያወገዙት ጳጳሱ፣ ይህንኑ እየገለጹ ባለበት ወቅት፣ ወታደሮች በፍጥነት ደርሰው ይዘዋቸው በመሄድ እስር ቤት አስገብተዋቸዋል።

ይህንኑ መረጃ ተከትሎ ወላጆች ልጆቻችንን ፍቱልን በማለት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ፖሊሶች ለወላጆቹ ጥያቄ መልስ አልሰጡም። ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ መሆኑንና ኮማንድ ፖስቱ የሚባለው አዲሱ ወታደራዊ አገዛዝ ብቻ እንደሚመለከተው መልስ ሰጥተዋል። በከተማው ሰሞኑን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ሰራዊት ገብቶ ከሰፈረ በሁዋላ በትምህርት ቤቶች ሳይቀር ፍተሻ እያካሄደ ነው። በዛሬው እለት ከ70 ያላነሱ ወጣቶች ታፍሰው ታስረዋል። ብዙዎቹ ወደ ብርሸለቆ ተወስደዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ራሳቸውን ያደራጁ ወጣቶች ሻለቃ መሳፍንት ጥጋቡ (ገብርየን) በማሰብ የሻመ ማብራት ስነስርዓት ማድረጋቸውንም የአካባቢው ወጣቶች ገልጸዋል።