ኢሳት (ህዳር 21 ፥ 2009)
የኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሆነው የገዳ ስርዓት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የአለም ወካይ ቅርስ ተደርጎ ተመዘገበ።
በአዲስ አበባ ከተማ አመታዊ ጉባዔውን እያካሄደ የሚገኘው ድርጅቱ ከገዳ ስርዓት በተጨማሪ የ10 ሃገራት ወካይ ቅርሶች የማይዳሰዱ ቅርሶች ሆነው እንዲመዘገቡ ማድረጉን በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘግበዋል።
የገዳ ስርዓት በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ዴሞክራሲንናና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ያስተዋወቀ በመሆኑ በድርጅቱ ሊመዘገብ መቻሉን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እልፍነሽ ሃይሌ ተናግረዋል።
ዩኔስኮ የገዳ ስርዓት የአለም ወካይ ቅርስ እንዲሆን አድርጎ መመዝገቡ ለረጅም ጊዜ የቆየው ባህሉ እንዲለማ እንዲጠበቅና ለትውልድ እንዲተላለፍ አሰተዋጽዖ የሚያደርግ መሆኑን ሃላፊዋ አስረድተዋል።
ባለፈው አመት አመታዊ ጉባዔውን በናሚቢያ አካሄዶ የነበረው ድርጅቱ የፍቼ ጨምበለላ ባህልን በተመሳሳይ መልኩ መዝግቦ እንደነበር ይታወሳል።
በቤልጂየም፣ ባንግላዴሽ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ አፍጋኒስታን፣ ኩባ፣ ግብፅ፣ ቻይና እና ስፔን ያሉ 10 ወካይ ቅርሶች አዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ባለው ጉባዔ በተመሳሳይ መልኩ መመዝገባቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ከሁለት አመት በፊት የመስቀል ደመራ ሃይማኖታዊ ስርዓት በዩኔስኮ መመዝገቡም የሚታወስ ሲሆን፣ ዕውቅናው የቱሪስት መስህብነት እንዲጨምር አስተዋጽዖ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።