ኢሳት (ህዳር 20 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን ጋር በምታዋስንበት የጋምቤላ ክልል ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል ማስፈሯ ተገለጠ።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ያለፈቃድ በጋምቤላ ክልል በኩል ወደ ሃገር ገብተዋል ስለተባሉ የአውሮፕላኖች ዘገባን ያቀረበው ጄኔራል አቪየሽን መጽሄት በጋምቤላ ክልል ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል ተሰማርቶ እንደሚገኝ አመልክቷል።
በቅርቡ በደቡብ ሱዳን በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ኢትዮጵያ ከሃገሪቱ ጋር በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ ወታደሮቿን ለማስፈር እንደተገደደች ታውቋል። በተለያዩ ጊዜያት የታጠቁ ሃይሎች በጋምቤላ ክልል ጥቃትን ሲፈጽሙ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስት በሪክ ማቻር ከሚመራው አማጺ ቡድን ጋር የፈጠረው አለመግባባት በስፍራው ውጥረት ማንገሱን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ወታደሮች በአካባቢው በብዛት መስፈራቸውን ያስነበበው ጄኔራል አቪየሽን መጽሄት የወታደሮቹ መሰማራት ከአማጺ ቡድኑ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ይሁን አይሁን ያመለከተው ነገር የለም።
ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር የደረሰችውን የሁለትዮሽ ስምምነት ተከትሎ የአማጺ ቡድኑ መሪ ማቻር ወደ ሃገሩ እንዳይገቡ ውሳኔን ያስተላለፈች ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰው የነበሩት የአማጺ ቡድኑ መሪ የመግቢያ ቪዛ አልያዙም ተብለው ወደ ተነሱበት ደቡብ አፍሪካ እንዲመለሱ መደረጉ ይታወቃል።
ማቻር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ መደረጉን ተከትሎ የሱዳን ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ ኢትዮጵያ ሪክ ማቻርን ከተደረሰው ስምምነት ውጭ ለማድረግ ጥረት እያደረገች ነው ሲል ድርጊቱን ማውገዙን መዘገባችን አይዘነጋም።
መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ አድርገው የነበሩት ሪክ ማቻር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር የደረሱት ስምምነት በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ ሲል ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የአማጺ ቡድኑ ዋና ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮችም በአካባቢው ሰፍረው እንደምገኙ ታውቋል።
ኢትዮጵያ በክልሉ ሰፈረው ይገኛሉ የተባሉትን ወታደሮች አስመልክቶ የሰጠችው ምላሽ የለም።