የብራዚል የእግር ኳስ አባላት ይዞ ይጓዝ የነበረ አውሮፕላን በኮሎምቢያ በመከስከሱ 76 ሰዎች ሞቱ

ኢሳት (ህዳር 20 ፥ 2009)

ከ80 በላይ የብራዚል የእግር ኳስ አባላትና መንገደኞችን ይዞ ይጓዝ የነበረ አውሮፕላን በኮሎምቢያ የመከስከስ አደጋ ደርሶበት 76 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተገለጠ።

ማክሰኞ ጠዋት አደጋ ያጋጠመው የመንገደኞች አውሮፕላን መነሻውን ከብራዚል አድርጎ በቦሊቪያ በኩል ወደ ኮሎምቢያ በማቅናት ላይ እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል። አንድ የብራዚል የእግር ኳስ ቡድን ሙሉ አባላትን ይዞ የነበረው ይኸው አነስተኛ አውሮፕላን በሰሜናዊ ምዕራብ ኮሎምቢያ ተራራማ አካባቢ በደረሰ ጊዜ አደጋው እንደደረሰበት ታውቋል።

የኮሎምቢያ የሲቪል አቪየሽን ተቋም ከአደጋው ስድስት ሰዎች ብቻ መትረፋቸውን አስታውቆ ከብራዚሉ የእግር ኳስ ቡድን አባላት ሁለት ተጫዋቾች ብቻ ሊተርፉ መቻላቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርጓል።

የብራዚሉ የእግር ኳስ ቡድን በደቡብ አሜሪካ ሲካሄዱ ለቆየው የክለቦች የማጠናቀቂያ ጨዋታ ላይ ለመገኘት በጉዞ ላይ የነበረ ሲሆን፣ ቡድኑ በብራዚል የእግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛ ተወዳጅነት እያገኘ የመጣ እንደነበር ቢቢዚ በዘገባው አመልክቷል።

የኮሎምቢያ ፖሊስ ኮማንደር የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል ጆሴ ጀራርዶ አደጋ ያጋጠመው አውሮፕላን የተከሰከሰበት ስፍራ ተራራማ በመሆኑ ምክንያት የነፍስ አድን ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል።

ይሁንና አውሮፕላኑ በምን ምክንያት አደጋው ሊደርስበት እንደቻለ እስካሁን ድረስ የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፣ የኮሎምቢያና የብራዚል ባለስልጣናት የጋራ ምርመራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

የብራዚሉ ፕሬዚደንት ሚቼል ቴመር በሃገሪቱ የሶስት ቀን የሃዘን ጊዜን ያወጁ ሲሆን፣ የእግር ኳሱ አዘጋጆቹ አደጋ የደረሰበት ቡድን ለመታሰቢያነቱ ዋንጫው እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

የቡድኑ ዋና ግብ ጠባቂ ማርኮ ፓዲሃ ከአደጋው ተርፎ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱ ማለፉን የኮሎምቢያ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በዚሁ አደጋ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከእግር ኳስ ቡድኑ ጋር ይጓዙ የነበሩ ደጋፊዎችም መሞታቸውን የብራዚል ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

የአደጋውን መድረስ ተከትሎ የደቡብ አሜሪካ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ሁሉንም ስፖርታዊ ውድድድሮች ሰርዟል።