በጋምቤላ ሲያለሙ የነበረውን መሬት ለመንግስት ያስረከቡ ባለሃብቶች መንግስት በጉዳዩ ላይ እልባት ባለመስጠቱ ቅሬታ አቀረቡ

ኢሳት (ህዳር 20 ፥ 2009)

በጋምቤላ ክልል በስህተት የእርሻ ቦታ ተሰጥቷችኋል ተብለው በማልማት ላይ የነበሩትን የመሬት ይዞታ እንዲያስረክቡ የተደረጉ ባለሃብቶች መንግስት ለአንድ አመት ያህል ዕልባት አልሰጠንም ሲሉ ቅሬታን አቀረቡ።

የግብርና ሚኒስቴር በሃገሪቱ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ለአባይ ግድብ ግንባታ በሚያደርጉት ድጋፍ ዙሪያ ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ የውይይት መድረክ ቢጠራም ተሳታፊዎቹ ለባለስልጣናት ተቃውሞ በማቅረባቸው ሳቢያ ውይይቱ ሳይሳካ መቅረቱን በሃገር ውስት ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በሚኒስቴር ዴኤታው ሰአዳ ከድር ሰብሳቢነት የተካሄደው ውይይት ዋነኛ አጀንዳው በአባይ  ግድብ ላይ የነበረ ቢሆኑም ከጋምቤላ ክልል ከእርሻ ኢንቨስትመንታቸው የተነሱ ባለሃብቶች አጀንዳውን ወደ ጎን በመተው ትኩረታቸውን በጥያቄያቸው ላይ ማድረጋቸው ታውቋል።

ለመንግስት ተወካዮች ቅሪታቸውን ያቀረቡት እነዚሁ ባለሃብቶቹ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብን ለልማት በማዋል ላይ እያሉ የተሰጣችሁ መሬት በስህተት ነው ተብለው ይዞታቸውን እንዲያስረክቡ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ባለፈው አመት 107 የሚደርሱ ባለሃብቶች በጋምቤላ ክልል የተሰጣችሁ መሬት በስህተት ነው ተብለው የእርሻ መሬታቸውን እንዲያስረክቡ መደረጉ ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ከተማን ግማሽ ያህል የቆዳ ስፋት በጋምቤላ ክልል ብቻ ተረክበው የነበሩት ባለሃብቶች መንግስት በወሰደው እርምጃ ኪሳራ እያደረሰባቸው እንደሆነ ይገልጻሉ። የመንግስት ባለስልጣናት ድርጊቱ ምርመራ ይካሄድበታል ቢሉም እስካሁን ድረስ የታየ ነገር አለመኖሩ ቅሬታን እንዳሳደረባቸው ባለሃብቶቹ አስታውቀዋል።

የፌዴራል ባለስልጣናት የጋምቤላ ክልል ለልዩ የኢኮኖሚ ዞን የተከለለን መሬት ያለአግባብ ሰጥተዋል በማለት የባለሃብቶቹ መሬት እንዲታገድ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በበኩሉ የተላለልፈውን ውሳኔ ተከትሎ በእርሻ መሬት ላይ ለተሰማራ ባለሃብቶች የሚሰጠውን ብድር እንዲሁም የመሬት የሊዝ ርክክብ እንዲቋረጥ ማድረጉ ይታወሳል።

የውጭ ኩባንያዎችን ጨምሮ ቁጥራቸው ያልታወቁ ባለሃብቶች በአንድ ይዞታ ላይ ከባንኩ ከፍተኛ ብድርን በመውሳድ በባንኩ ላይ ኪሳራ ማድረሳቸውን ባንኩ ሲገልጽ ቆይቷል።

በክልሉ በአንድ ይዞታ ላይ በተደጋጋሚ ብድርን ወስደዋል የተባሉ የህንድ ኩባንያዎች የወሰዱትን ብድር ሳይመለሱ ከሃገር የኮበለሉ ሲሆን፣ መንግስት ብድሩን ለማስመለስ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል ሲል በቅርቡ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል ብቻ ተፈጽሟል በተባለው የአሰራር ክፍተት በሚሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ኪሳራ እንደደረሰበት አረጋግጧል።

ይሁንና በርካታ ባለሃብቶች በውሳኔው ያለ አግባብ ጉዳት ደርሶብና በማለት ቅሬታን እያቀረቡ ሲሆን፣ መንግስት በበኩሉ በጉዳዩ ላይ እየተካሄደ ያለ ጥናት ሲጠናቀቅ ለባለሃብቶቹ ምላሽን እንደሚሰጥ ይገልጻል።

ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደው መድረክ የተሳተፉት ባለሃብቶች በአባይ ግድብ ግንባታ ላይ እንዲወያዩ የተጠራውን መድረክ ወደ ጎን በመተው ለቅሬታቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ማሳሰባቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ከባለሃብቶቹ ድጋፍን ለማሰባሰብ መድረኩን አዘጋጅቶ የነበረው የግብርና ሚኒስቴር ከአጀንዳ ውጭ በቀረበበት ጥያቄ ምክንያት የጠራው ውይይት ሳይሳካ ቀርቷል።