ወደ የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እንዳሳሰበው ተመድ ገለጸ

ኢሳት (ህዳር 20 ፥ 2009)

ጦርነት እልባት ወዳላገኘባት የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ስጋት አሳድሮበት እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ማከሰኞ ገለጸ።

አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑት 106ሺ ስደተኞች በተያዘው የፈረንጆቹ 2016 አም ወደ የመን መሰደዳቸውን ኮሚሽኑ ያስታወቀ ሲሆን፣ ቁጥሩ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ13ሺ በልጦ መገኘቱ ታውቋል።

ወደ የመን ለመሰደድ ሙከራን ካደረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያና የሶማሊያ ስደተኞች መካከል በትንሹ 79 ስደተኞች በተያዘው ዓመት ብቻ መሞታቸውን የስደተኞች ድርጅቱ ከዋናው ቢሮ ስዊዘርላንድ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በስደተኞቹ ላይ በየመን የሚደርሰው አደጋ እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከቀጣዩ ወር ጀምሮ የስደተኞቹ ጉዞ እንዲቀንስ ለማስቻል አህጉራዊ ዘመቻ እንደሚጀመር ይፋ አድርጓል።

በቅርቡ የየመን ባለስልጣናት ወደ ጎረቤት ጅቡቲ ካሰፈሯቸው ከ70 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል ከ20 የሚበልጡት ህይወታቸው ማለፍ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ጦርነት ዕልባት ወደአላገኘባት የመን የሚሰደዱበት ምክንያት ግልጽ እንዳልሆነላቸው ሲገልጹ ቢቆዩም ድርጊቱ አሁንም ድረስ መቀጠሉ ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረባቸው አክለው አመልክተዋል።

የስደተኛ ኮሚሽኑ ቃል አቀባይ የሆኑት ዊሊያም ስፒንድለር ስደተኞቹ የመን ከገቡ በኋላ እየተካሄደ ካለው ጦርነት በተጨማሪ የተለያዩ ችግሮች እየደረሱባቸው መሆኑን ለVOA የእንግሊዝኛው ክፍል አስረድተዋል።

አብዛኞቹ የኢትዮጵያና የሱማሌ ስደተኞች ወደ የመን ከገቡ በኋላ ጉዞአቸውን ወደ ሳውዲ አረቢያና ሊቢያ በማድረግ ወደ አውሮፓ የመሄድ እቅድ እንዳላቸው ይነገራል።

ይሁንና፣ በየመን ያለው የርስ በርስ ጦርነት ስደተኞቹ ካሰቡበት ቦታ እንዳይደርሱ በማድረግ ሞትን ጨምሮ ለተለያዩ ስቃዮች እየዳረጋቸው መሆኑን የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን ባለስልጣናት ይገልጻሉ።