ስዊድን በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ የዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ገለጸች

ኢሳት (ኅዳር 19 ፥ 2009)

ስዊድን በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጋዋ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ስጋት እንዳሳደረባት ገለጸች።

የስዊድን ዜግነት ያላቸውና የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ላይ ለመስራት ከጥቂት አመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የነበሩት ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ከሶስት አመት በፊት ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።

በፌዴራል አቃቤ ህግ የተመሰረተባቸውን ክስ ሲከታተል የነበረው ፍርድ ቤት ባለፈው ወር የህክምና ባለሙያው በአራት አመት ከስምንት ወር እስራት እንዲቀጡ ውሳኔን አስተላልፏል።

ጉዳዩን በመከታተል ላይ የሚገኘው የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ አብዛኛውን የቅጣት ጊዜያቸውን በእስር ቤት በማሳለፋቸውና በቆይታቸው ጥሩ ስነምግባር በማሳየታቸው በተያዘው ወር ይፈታሉ ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር ሬዲዮ ስዊድን ሰኞ ዘግቧል።

ይሁንና የልብ ቀዶ ሃኪሙ በእስር ቤት በሚገኙበት የቂሊንጦ እስር ቤት ከወራት በፊት ደርሶ ከነበረው የእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ አዲስ ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሆነ ጠበቃቸው ሃንስ ባግነት ለስዊድን መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ከሳሽ አቃቤ ህግ ባለፈው 38 እስረኞች በቂሊንጦ እስር ቤት ደርሶ ለነበረው የእሳት አደጋ ተጠያቂ ናቸው ሲል አዲስ ክስ መመስረቱ የሚታወስ ነው።

የልብ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ላይ ለመሰማራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡትና ከተመሰረተባቸው የሙስና ክስ በቅርቡ ይለቀቃሉ ተብለው ይጠበቁ የነበረው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ከ38ቱ ተከሳሾች መካከል አንዱ መሆናቸውን የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ጠበቃቸው ይፋ አድርገዋል።

ይሁንና በዜጋው የጤና ሁኔታ ስጋት እንዳደረበት ያሳወቀው የስዊዲን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መነጋገር መጀመሩን የሚኒስቴሩ ተወካይ ፓትሪክ ኒልሰን ለራዲዮ ስዊድን አስረድተዋል።

የተካሳሹ ጠበቃ የሆኑት ሃንስ ባግነት በበኩላቸው ደንበኛቸው ከሃገር እንዳይወጡ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው በመግለጽ አዲሱ ክስ ደንበኛቸው ከእስር የመፈታታቸውን ጉዳይ ውስብስብ አድርጎት እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የፌዴራሉ ከሳሽ አቃቤ ህግ ከአራት አመት በፊት የገቢዎችና ጉምሩክ ሚኒስቴር የነበሩትን አቶ መላኩ ፋንታን ጨምሮ ከ60 የሚበልጡ ባለሃብቶችን ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ለእስር መዳረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ በዚሁ ክስ ውስጥ አንዱ መሆናቸው ታውቋል።

ከሳሽ አቃቤ ህግ ከ20 የሚበልጡ እስረኞች ለሞቱበት የቂሊንጦ የእስር ቤት የእሳት ቃጠሉ አደጋ 38 እስረኞችን ተጠያቂ በማድረግ እስረኞቹ ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት ሲያደርጉና ገንዘብ ሲቀበሉ ነበር ሲል በክሱ አስፍሯል።