በዩጋንዳ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ55 ሰዎች በላይ ተገደሉ

ኢሳት (ኅዳር 19 ፥ 2009)

በዩጋንዳ መንግስትና በታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በትንሹ 55 ሰዎች መገደላቸውንና በድርጊቱ በሃገሪቱ ውጥረት ማንገሱ ተገለጠ።

የዩጋንዳ ፖሊስ በበኩሉ ቅዳሜ የተከሰተውን ይህንኑ ግጭት ተከትሎ ከድርጊቱ ግንኙነት ያላቸው የጎሳ ንጉስ ለእስር መዳረጉን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የርዌንዙሩሩ ጎሳ ንጉስ ቻርለስ ዊስሊ ምምቤሬ ለሁለት ቀን ዘልቆ ከነበረው ግጭት ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው አስተባብለዋል።

በዩጋንዳ የጸጥታ ሃይሎችና ንጉሱን ይደግፋሉ በሚባሉ ታጣቂዎች በተካሄደው መጠነ-ሰፊ ግጭት በንሹ 14 የፖሊስ አባላትና እና 41 ታጣቂዎች መገደላቸውን የዩጋንዳ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

የዩጋንዳ መንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ሻባን ባንታሪዛ ሃገሪቱን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር በሚያዋስናት አካባቢ የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች ራሳቸውን ከዩጋንዳ በመገንጠል ነጸ ግዛት ለማቋቋም ይታገላሉ ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የዩጋንዳ መንግስት የጸጥታ ሃሎች ታጣቂዎቹና ንጉሱ ግንኙነት አላቸው በማለት የንጉሱን ቤተ-መንግስት  እሁድ በመውረር በርካታ ሰዎችን ለእስር የዳረገ ሲሆን፣ የጎሳ ንጉሱም ወደ መዲናይቱ ካምፕላላ መወሰዳቸው ታውቋል።

ንጉሱ የሚመሩት የባኮንዞ ማህበረሰብ በኮንጎ ድንበር አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን፣ በአካባቢው የበላይነት አላቸው ከሚባሉት የቶሮ ጎሳ አባላት ጋር አለመግባባት ውስጥ እንደሚገኙ ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።

ለእስር የተደረጉት ንጉስ ምምቤሬ ለፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ መንግስት ተቀናቃኝ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ንጉሱ በሚገኙበት የምዕራብ ዩጋንዳ አካባቢ ሙሴቬኒ በሶስት ብሄራዊ ምርጫዎች ቢወዳደሩም በሶስቱም ጊዜ ሽንፈት እንደደረሰባቸው የዩጋንዳ መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል።

የንጉሱ ለእስር መዳረግ በዩጋንዳ አዲስ የፖለቲካ ውጥረትን ያስከትላል ተብሎ መሰጋቱን የሃገሪቱ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።

አልጀዚራ የቴለቪዥን ጣቢያ በበኩሉ የንጉሱ መታሰር ተከትሎ በአካባቢው የተቀሰቀሰውን ግጭት እልባት አለማግኘቱንና ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የአዲስ ግዛት ምስረታ መቼም ቢሆን እንደማይፈቅዱ መግለጻቸውን ዘግቧል።

ታጣቂዎቹ ይራ (Yiira) የሚባል ሪፐብሊክ የመመስረት አላማ እንዳላቸው ይነገራል። ፕሬዚዳንቱ በአካባቢው ላለው ውጥረት እልባት ለመስጠት ለንጉሱ ሰባት አመት በፊት እውቅናን ቢሰጡም እርምጃውን ሰላም ሊያመጣ አልመቻሉን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።