ኢሳት (ኅዳር 16 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ መውጣታቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ልዑክ በአልሸባብ ታጣቂ ቡድን የተያዙ ቦታዎችን ነጻ ለማውጣት ተጨማሪ ከ40ሺ በላይ ወታደሮች እንደሚያስፈልጉት ገለጸ።
የሰላም አስከባሪ ልዑክ በአሁኑ ሰዓት ወደ 21ሺ አካባቢ የሰላም አስከባሪ አባላት ቢኖሩትም ሁሉንም የአልሸባብ ይዞታዎችን ለመቆጣጠርና መልሶ ለመያዝ አለመቻሉን የልዑኩ ሃላፊዎች ዋቢ በማድረግ ዘ-ኢስት አፍሪካን የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
የልዑኩ ቃል አቀባይ የሆኑት ኮሎኔል ጆሴፍ ኪቤት ተጨማሪ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች በጁባ የስምጥ ሸለቆ ባኮል፣ ሂራንና፣ ዙሪያ ያሉ ቦታዎችን ከታጣቂ ቡድኑ አልሸባብ መልሶ ለመያዝ እገዛን እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ካለፈው ወር ጀምሮ ከእነዚሁ ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው የወጡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ዕርምጃው የተወሰደው በሎጂስቲክ ችግርና ለስልት እንደሆነ ገልጻለች።
ኬንያ፣ ቡሩንዲ፣ ማላዊ፣ በሶማሊያ አሰማርተው የሚገኙትን የሰላም አስከባሪ ሃይል ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ለማስወጣት እቅድን የያዙ ሲሆን፣ ድርጊቱ ለታጣቂ ሃይሉ መጠናከር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ተሰግቷል።
ኢትዮጵያ በሰላም አስከባሪ ልዑክ ስር ካሰማራቻቸው ወደ 4ሺ ወታደሮች በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ የተናጥል ወታደሮችን በተለያዩ የሶማሊያ ግዛቶች አሰማርታ መቆየቷ ይታወቃል።
መንግስት የእነዚህን ወታደሮች ቁጥር ከመግለጽ ቢቆጠብም በደህንነት ዙሪያ ዘገባዎችን የሚያቀርብ አንድ ተቋም ሰሞኑን ከሶማሊያ ለቀው የወጡ የኢትዮጵያ ወታደሮቹ ቁጥር ወደ 12ሺ አካባቢ እንደሚገመት ይፋ አድርጓል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ወታደሮች ካለፈው ወር ጀምሮ ከሶማሊያ ለቀው የወጧቸው ከተሞች ወደ 100 መድረሱን አልጀዚራ ዘግቧል።
የወታደሮቹ መውጣት ተከትሎም አልሸባብ ታጣቂ ቡድን ሁሉንም ከተሞች መቆጣጠሩ ተመልክቷል።
ከተሞቹንና ቁልፍ ወታደራዊ ዞታዎችን ተቆጣጥሮ የሚገኘው አልሸባብ በአሁኑ ወቅት ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር ምክክርን በማካሄድ ከኢትዮጵያ ወታደሮች እና ከሶማሊያ መንግስት ጋር ተባብረው ይሰሩ የነበሩ የጸጥታ አባላት ከህብረተሰቡ ጎን በሰላማዊ መንገድ እንዲኖሩ እያደረገ መሆኑን የቴሌቪዥን ጣቢያው አመልክቷል።