ወታደራዊ እዙ ( ኮማንድ ፖስት) በአዳማ ተቃውሞ ገጠመው

ኅዳር ፲፭ (አሥራ አምስት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ባለፈው ሳምንት ከሰኞ እስከ ዓርብ ኢህአዴግና የከተማው መስተዳድር በአዳማ ከተማ ከኢህአዴግ አባላትና ደጋፊ የከተማው ነዋሪዎች ጋር ስለ ወታደራዊ እዙ ተግባርና ኃላፊነት፣ ስለተደረገው ሹም ሽር እንዲሁም የክልሉንና የከተማዋን ልማትና ጸጥታ ሁኔታ በሚመለከት በተደረገው ስብሰባ ላይ ያልተጠበቀ ተቃውሞ ተነስቷል።

በዚህ መድረክ የተሳተፉት የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ቢሆኑም የከተማዋ የኮማንድ ፖስት ኃላፊ ማንነት እንደተገለጸ ብዙዎች የተቃውሞ ድምጻቸውን በጩኸት አሰምተዋል።  ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል፡፡ የ‹‹ ኮማንድ ፖስት ኃላፊ›› ሆነው የተሾሙት አቶ አብረሃም ከዚህ በፊት በከተማዋ አስተዳደር የቢሮ ኃላፊ እያሉ በከተማው ህዝብ በጭካኔኣቸው፣ የህዝብን ጥያቄ በማፈን፣እንዲሁም በሙስና የተዘፈቁ፣በአጠቃላይም በግፍ ድርጊታቸው የሚታወቁና ‹ነፍሰ በላው› በሚል ቅጽል ሥም የሚጠሩ ናቸው፡፡አቶ አብርሃ ለወታደራዊ ጥርነፋው አዛዥ ሆነው መመደባቸው ነዋሪዎችን ለማሰቃየት እና አፈናውን ለማጠናከር የታቀደ እንጂ ለተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ሰላማዊና ህጋዊ መፍትሄ ለማምጣት አይደለም ››ሲሉ ተሰብሳቢዎች ገልጸዋል። በከተማዋ አስተዳደር የተደረገው ሹም ሽርና አዲሱ ሹመትም እያነጋገረ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡

ነዋሪዎች እንደሚሉት አቶ ካሳሁን ጎንፌ የናዝሬት ምክትል ከንቲባ ሆነው መሾማቸው ህዝቡን አስቆጥቶታል፡፡ አቶ ካሳሁን ጎንፌ ቀድሞ  የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሠራተኛ የነበሩ ሲሆን፣ የከተማ ልማትና ቤት ሚኒስትር የነበሩት አቶ መኩሪያ ኃይሌ የሚኒስቴሩ የኮሚኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይረክተር አድርገው ሾመዋቸው ነበር። ይሁን እንጅ በመስሪያ ቤቱ ሴት ሰራተኞች ላይ በሚፈጽሙት በደልና በተጭበረበረ መንጃ ፈቃድ ያለችሎታ የመ/ቤቱን መኪናዎች ደጋግመው በማጋጨት በንብረትና አካል ላይ አደጋ በማድረስ ተገምግመው በምግባረ ብልሹነት ወደነበሩበት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት  እንዲመለሱ  ተደርገዋል።

“ አቶ ካሳሁን ጎንፌ  የአዳማ ከተማ ም/ከንቲባ ሆነው መሾማቸው ለከተማው ህዝብ ንቀት ነው›› በማለት ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ቀርቦባቸው የነበሩት የከተማው ከንቲባ ከስልጣን ተነስተው  የቦረና ዞን አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመዋል።

በሌላ ዜና ደግሞ በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ ያለው ውጥረት እንደቀጠለ ነው። የከተማው ፖሊሶች ከሌላ አካባቢ ከመጡ የኮማንድ ፖስትአባላት ጋር ሊግባቡ አለመቻላቸው ለውጥረቱ መጨመር ምክንያት ሆኗል። የአካባቢው ፖሊሶች “ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ እንድንወስድ ይፈለጋል፣ እኛ ደግሞ ይህን ማድረግና ከህዝባችን መጋጨት አንፈልግምና በዚህ ምክንያት በመካከላችን መግባባት ጠፍቷል ፤ ከዕለት-ዕለት ልዩነቱ እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው”  በማለት ይናገራሉ።

በሌላ በኩል በከተማው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት/ኦህዲኅ/ አመራር አባላት እነ መምህር ዓለማዬሁ መኮንን  ህዳር 12/ 2009 ዓም ከታሰሩበት የከተማው ፖሊስ ጣቢያ ወደ ዞኑ ፖሊስ መምሪያ መወሰዳቸው ታውቋል፡፡

የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት አባልና የዞን አመራር የነበሩት አቶ አኮ ባይሲኖ  በትናንተናው ዕለት  ተይዘው ታስረዋል።