በሱዳን ካርቱም ከተማ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ

ኢሳት (ኅዳር 15 ፥ 2009)

በሱዳን የተከሰተን የሸቀጣሸቀጦች ዋጋ ንረት ተከትሎ በርካታ ተማሪዎች ሃሙስ በመዲናይቱ ካርቱም የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።

የሃገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች የተቃውሞ ሰልፍን ለመበተን በወሰዱት ዕርምጃ፣ ግጭት ተቀስቅሶ ቁጥራቸው ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል ።

ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ተማሪዎች የሱዳን መንግስት የሸቀጣቀጦች ዋጋ ንረት እንዲረግብ እርምጃን መውሰድ እንዳለበት መጠየቃቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። khartoum-01

መንግስት በተለይ በነዳጅ ምርቶች ላይ ሲያደርግ የቆየውን ድጎማ ማንሳቱ በሱዳን መድሃኒትን ጨምሮ የተለያዩ መሰረታዊ አገልግሎት ሸቀጣሸቀጦች ዋጋ መናሩን ሰልፈኞቹ አስታውቀዋል።

የፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር መንግስት በነዳጅ ምርት ላይ የወሰደውን የማስተካከያ ዕርምጃ ተከትሎ በነዳጅ ዋጋ ላይ የ30 በመቶ ጭማሪ መታየቱን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።

ይህንኑ የዋጋ ንረት በመቃወም አደባባይ የወጡ የሱዳን ተማሪዎች በመንግስት ላይ የተቃውሞ ድምጾችን ሲያሰሙ እንደነበርም ታውቋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህዝባቸውና ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከፍተኛ ቅሬታ እየቀረበባቸው የሚገኙት ፕሬዚደንት አልበሽር የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸው ይነገራል።

በተያዘው ሳምንት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራት በዝግጅት ላይ ነበሩ የተባሉ ከ10 በላይ የፓርቲ አባላት ለእስር መዳረጋቸውን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

በአፍሪካ ለረጅም አመታት በስልጣን ላይ ከቆዩ መሪዎች አንዱ የሆኑት አልበሽር በሃገራቸው አፈናን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን አባብሰዋል ተብለው ከተለያዩ አለም አቀፍ አካላት ትችት እየቀረበባቸው ይገኛል።

ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚደንቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሃገራቸው ተቃውሞ እየበረታባቸው ሲሆን፣ ህዝባዊ ተቃውሞን ለማርገብ የሃይል ዕርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ የሱዳን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይገልጻሉ።

ሃሙስ በመዲናይቱ ካርቱም በተማሪዎች በተካሄደው ተቃውሞ ወቅት ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል ተሰማርቶ የነበረ ሲሆን፣ ትዕይንቱ የህዝብ ቅሬታን ያንጸባረቀ እንደነበር ተገልጿል።

የሱዳን አቃቤ ህግ በበኩሉ 26 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ክስ ሊመሰርትባቸው እንደሚችል ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።