ኅዳር ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በቲቶ ፉርጊሳ የምህንድስና ትምህርት ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች የጀመሩትን ተከታታይ ተቃውሞ ተከትሎ፣ ወታደሮች ተማሪዎችን ከምሽቱ 2 ሰአት ላይ በማውጣት እስከ ሌሊቱ 11 ሰአት ድረስ እየደበደቡ ከፍተኛ ኢ ሰብአዊ ድርጊት ፈጽመዋል።
የኮማንድ ፖስትን በመወከል ተማሪውን ዛሬ የሰበሰቡ አካላት ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። እንደ ተማሪዎቹ ገለጻ የኮማንድ ፖስት ወኪሎች ‹‹ አርፈን አንማርም ካላችሁና በረብሻው ከቀጠላችሁ እንጨርሳችኋለን፤ ብትጠነቀቁ መልካም ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ለናንተ ጥጋብ ትዕግስት የለንም፡፡›› ያሉ ሲሆን፣ አንዳንድ ሴት ተማሪዎች በስብሰባው ወቅት ራሳቸውን ስተዋል።
ተማሪዎቹን ለማንሳትና ለመርዳት የሞከሩ ሌሎች ተማሪዎችን ‹‹ተዋቸው፣ እንዳታነሷቸው፤ የራሳቸው ጉዳይ ›› በማለት ያስፈራሩት ታጣቂዎች በቁመናቸውና በአለባበሳቸው እንዲሁም በሚያሳዩት እንቅስቃሴ በወጣቶቹ ላይ ከፍተኛ የስነ ልቦና ጨና ሲፈጥሩ ውለዋል፡፡
ይሁንና ስብሰባው እንዳበቃና በመደበኛ ግቢው ካለው ኃይል በተጨማሪ የገባው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታጣቂ ኃይል ግቢውን ለቆ እንደወጣ የተማሪዎቹ ተቃውሞው ቀጥሏል፡፡