በሃረር በርካታ ዜጎች ሲታሰሩ በባህርዳር ደግሞ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ኅዳር ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በመጪው ህዳር 29 ቀን 2009 ዓም ከሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች በአል ጋር በተገናኘ ይሁን አይሁን ባይታወቅም፣ በሃረር ከተማ ከፍተኛ ፍተሻ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ በፍተሻ ወቅት የክልሉን መታወቂያ ያልያዙ ሰዎች እየተያዙ ወደ እስር ቤት ተወስደዋል። ከሌሎች ክልሎች ሄደው በክልሉ ውስጥ በመስራት ላይ ያሉ በርካታ ዜጎች፣ የክልሉን መስተዳድር መታወቂያ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፣ ከመጣችሁበት ክልል መሸኛ አምጡ በመባላቸው መታወቂያ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። እነዚህ ዜጎች በፍተሻ ወቅት የክልሉን መታወቂያ ማሳየት ባለመቻላቸው እየታሰሩ መሆኑን የክልሉ ወኪላችን ገልጿል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ታስረው የሚገኙ ሲሆን፣ ውዝፍ ግብር አልከፈሉም የተባሉ ከ50 በላይ ነጋዴዎችም ተይዘው ታስረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በባህርዳር ከተማ  በቅርቡ  በቦንብ ፍንዳታ ተጠርጥረው ከታሰሩት ወጣቶች መሀል አንዱ ለህክምና በሚል ሆስፒታል ላይ  ከጠባቂው ፓሊስ ጋ መጥፋቱ ያበሳጫቸው የወታደራዊ እዝ መሪዎች ፣ ዛሬ በ1ኛ ፓሊስ ጣቢያ የሚገኙትን ሀላፊ እና ተራ ፓሊሶች አስረዋል ።

ከታሰሩት መካከል ኢንስፔክተር ይብሬ ፣ ም/ ኢንስፔክተር ክብረ፣  ሃምሳ አለቃ አበበ፣ ኮንስታብል ወርቁ ይገኙበታል።