በቂሊንጦ እስር ቤት በእሳት ቃጠሎ እና በጥይት ለተገደሉ ታራሚዎች ሞት 38  እስረኞች ተጠያቂ ሆኑ

ኅዳር ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ባለፈው ዓመት ነሃሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ሆን ተብሎ የእሳት ቃጠሎ እንዲነሳ በማድረግ ከእሳቱ ለመሸሽ ሲያመልጡ የነበሩ ታራሚዎች በእሳት ቃጠሎ እና በግፍ በጥይት ተደብድበው መገደላቸው የሚታዉቅ ሲሆን ለዜጎች ሞት ምክንያት ናቸው የተባሉ 38 እስረኞች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ዛክስ ተመስርቶባቸዋል።

እስረኞቹ ሆን ብለው እሳት እንዲነሳ ያደረጉት በድብቅ የኦነግ፣ ግንቦት ሰባት እና አልሸባብ የሽብር ቡድኖችን ተልዕኮ ለማስፈፀም መሆኑን አቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል። በመሆኑም 1ኛ  ተከሳሽ ማስረሻ ሰጤ፣ 2ኛ ተከሳሽ ወልዴ ሞቱማ፣ 3ኛ ተከሳሽ አሸናፊ አካሉን ጨምሮ 38 እስረኞች ላይ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ ከሰው ህይወት መጥፋት በተጨማሪ ለ10 ሚሊዮን ብር የንብረት ውድመት እንዲፈጸም ምክንያት መሆናቸውንም እና በተለያየ ጊዜ በድብቅ መረጃ በመለዋወጥ የአመጽ ጥሪ በማስተላለፍ በማረሚያ ቤቱ አመጽ  የማስነሳት የሚሉ ክሶችን አቃቤ ሕግ በክስ ቻርጁ አስነብቧል። አብዛኞቹ ተከሳሾች በህግ በተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ የቆዩ ናቸው። ምርጫ 2007ትን ተከትሎ ገዢው ፓርቲ ህዝብን ሊያነሳሱ ይችላሉ በማለት ያሰራቸው እነዚህ ሰዎች፣ አሁን በእስር ቤቱ ለተነሳው ቃጠሎ ምክንያት ሆነው መቅረባቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

በእስር ቤቱ ታስረው የተፈቱ አንዳንድ ሰዎች እንደገለጹት እሳቱን ሆን ብለው ያስነሱት የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ናቸው። በተለይም ከወልቃይት ጠገዴ የአማራ ምንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ፣ ከተለያዩ እስር ቤቶች ተሰብስበው ወደ ቂሊንጦ እንዲገቡ በተደረገ በቀናት ውስጥ ቃጠሎው መነሳቱና አብዛኛው የቃጠሎውና የተኩሱ ሰለባ እነዚህ እስረኞች መሆናቸው ድርጊቱ በገዢው ፓርቲ ሰዎች የተቀነባበረ መሆኑን አመላካች ነው በማለት ይናገራሉ።