ኢሳት (ኅዳር 14 ፥ 2009)
እድሜ ጠገብ በሆኑ አውሮፕላኖች በሚደረገ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረ አንድ የብሪታኒያ ፓይለት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ከገባ በኋላ የገባበት አለመታወቁን የውድድሩ አዘጋጆች ረቡዕ አስታወቁ። የ72 አመቱ ሞሪስ ኪርክ የአፍሪካ ጉዞን በሚሸፍነው ውድድሩ ከጎረቤት ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል በመጓዝ ላይ እያለ ግንኙነቱ ተቋርጦ ያለበት ሁኔታ አለመታወቁን ዴይሌ ሜይል ጋዜጣ ዘግቧል።
የ72 አመቱ ፓይለት በውድድሩ እያለ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1940ዎቹ የተሰራችው አውሮፕላን ሞተሯ የቴክኒክ ችግር አጋጥሟት እንደነበር ተገልጿል።
ሞሪስ ኪርክ በቴክኒክ ችግር ውድድሩን እንዲያቋርጥ ቢነገረውም የአዘጋጆቹን ማስጠንቃቂያ ወደጎን በመተው በረራውን ቀጥሎ እንደነበር አዘጋጆች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የገባበት ያልታወቀውን ብሪታኒያዊ ፓይለት ጨምሮ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ከግሪክ እስከ ደቡብ አፍሪካ የሚሸፍነውን ጉዞ ለማድረግ ከቀናት በፊት ውድድራቸውን ጀምረው እንደነበር ታውቋል።
ይሁንና የ72 አመቱ ተወዳዳሪ ያጋጠመው አደጋ ለአዘጋጆች ስጋትን የፈጠረ ሲሆን፣ ፓይለቱ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ የተደረጉ ጥረቶች ሊሳኩ አለመቻላቸውን የብሪታኒያው ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።
ማክሰኞች ከጎረቤት ሱዳን መዲና ካርቱም ጉዞን ጀምሮ የነበረው ፓይለቱ መዳረሻው ውድ ሆነው የጋምቤላ ክልል ያርፋል ተብሎ ቢጠበቅም ምንም መረጃ ሊገኝ አለመቻሉን አዘጋጆች አክለው አስታውቀዋል።
“በውድድሩ ተሳታፊ የሆንነው ፓይለቶች በጓደኛችን ደብዛ መጥፋት ከፍተኛ ስጋት አድሮብናል” ሲሉ የኪርክ ጓደኛና የውድድሩ ተሳታፊ ማይክ ፍላይን ለዴይሊ ሜይል ጋዜጣ ገልጿል።
የውድድሩ አዘጋጆች የፓይለቱን መጥፋት አስመልክቶ ለኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን ቢያሳውቁም እስከ ረቡዕ ድረስ ምንም መረጃ ሊገኝ አለመቻሉን የውድድሩ አዘጋጆች አስታውቀዋል።
10 ሃገራትን የሚሸፍነው ይኸው የአፍሪካ የውድድር ለተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ገቢን ለማሰባሰብ የተዘጋጀ እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል።