ሪክ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ የተደረገው የመግቢያ ቢዛን ማግኘት ስላልቻሉ ነው ተባለ

ኢሳት (ኅዳር 14 ፥ 2009)

የደቡብ ሱዳን አማጺ ቡድን መሪ ሪክ ማቻር ከቀናት በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ የተደረገው የኢትዮጵያ የመግቢያ ቢዛን ማግኘት ስላልቻሉ ነው ሲል የአማጺ ቡድኑ አመራሮች ረቡዕ አስታወቁ።

የአማጺ ቡድኑ ሃላፊዎች ሪክ-ማቻር በኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል መባሉን በማስተባበል ድርጊቱ ቪዛን ቀድሞ ካለማግኘት ጋር የተፈጠረ ሁኔታ ነው ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአማጺ ቡድኑ አመራሮች ማቻር ለአራት ሰዓታት ከግማሽ ያህል በቁጥጥር ስር ውለው ወደ መጡበት ደቡብ አፍሪካ እንዲመለሱ መደረጉን ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።  rick-machar

ተመሳሳይ ማብራሪያን የሰጡት የሱዳን ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ አመራሮች ማቻር አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ደርሰው ቢዛ ማግኘት ባለመቻላቸው ምክንያት ወደ መጡበት ሃገር ሊመለሱ መገደዳቸውን አስረድተዋል።

ይሁንና ለአንድ አመት ያህል ጊዜ በአዲስ አበባ ቆይታ የነበራቸው ሪክ ማቻር በምን ምክንያት የመግቢያ ቢዛ ሊከለከሉ እንደቻለ የአማጺ ቡድኑም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።

የአማጺ ቡድኑ አመራሮች ማቻር በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት ለህክምና ጉዳይ ነው በማለት በኢትዮጵያ በኩል ወደ ደቡብ ሱዳን ለመጓዝ የነበራቸው እቅድ በቅርቡ በተደረሰ የሰላም ስምምነት ላይ ለመምከር እንደነበር አክለው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በቅርቡ ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር የደረሰችውን ስምምነት ተከትሎ የአማጺ ቡድኑ መሪ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ እገዳ መጣሏ ይታወሳል።

ይሁንና ሪክ ማቻር በኢትዮጵያ ነጻ የማረፊያና ሌሎች አገልግሎቶች ተሰጥቷቸው ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ድርድር ሲያካሄዱ ቆይተዋል።

በሁለቱ ወገኖች የተካሄደን ውይይት ተከትሎም ማቻር የምክትል ፕሬዚደንት ስልጣን እንዲያገኙ መደረጉም የሚታወቅ ነው።

በቅርቡ በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ በመንግስትና በአማጺ ቡድኑ መካከል የተቀሰቀሰን ግጭት ተከትሎ ሪክ ማቻር ወደ ጎረቤት ሱዳን ቀጥሎም ደቡብ አፍሪካ መግባታቸውን ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ ጋዜጣ በዘገባው አስነብቧል።

የማቻር አማጺ ቡድን የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ አልተደረገም በማለት በመንግስት ላይ አዲስ የትጥቅ ትግል ለማካሄድ ውሳኔን አስተላልፏል።