ኢሳት (ኅዳር 14 ፥ 2009)
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስትና ራሳቸውን ባደራጁ ሃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለውን ግጭት ተከትሎ የብሪታኒያ መንግስት ዜጎቹ እጅግ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር በክልሉ በሚገኙ አምስት ዞኖች እንዳይጓዙ አሳሰበ።
የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ለዜጎቹ ባሰራጨው መረጃ ወደ አገው አዊ፣ ባህር ዳር፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ጎንደርና በደቡብ ጎንደር ዞን አካባቢዎች የጥንቃቄ ዕርምጃ እንዲደረግ ባሰራጨው መግለጫ አመልክቷል።
የብሪታኒያ መንግስት በኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት የጉዞ ማሳሰቢያን ሲያወጣ የቆየ ሲሆን፣ ረቡዕ በአዲስ መልክ ባሰራጨው መረጃው ለአማራ ክልል ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ለመረዳት ተችሏል።
ሰሞኑን በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ራሳቸውን ያደራጁ ሃይሎች ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጋር ውጊያ ሲካሄዱ መሰንበታቸውን ዕማኞች ለኢሳት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
መንግስት በዚሁ ግጭት ዙሪያ ምላሽን ባይሰጥም የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሃገሩ ዜጎች እጅግ አስፈላጊ ካልሆነ ስራ በስተቀር ከላይ ወደተጠቀሱት ስፍራዎች ከመጓዝ እንዲታቀቡ አሳስቧል።
በቅርቡ የብሪታኒያ መንግስት የወሰደውን ተመሳሳይ ዕርምጃ ተከትሎ መቀመጫቸውን በሃገሪቱ ያደረጉ በርካታ አለም አቀፍ አስጎብኚ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርጉ የነበረን የጉዞ ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ መሰረዛቸው የሚታወስ ነው።
መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄዱ የነበሩ ተቃውሞዎች ዕልባት አግኝተዋል ቢልም የብሪታኒያ መንግስት ሃሙስ በአዲስ መልክ ባሰራጨው የጉዞ ማሳሰቢያ ተመሳሳይ ዕርምጃ በኦሮሚያ ክልል የምስራቅና ምዕራብ ሸዋ እንዲሁም በአርሲ ስር በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች እንዲወስድ ጠይቋል።
ባለፈው ወር ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ሃገሪቱ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ ማሳሰቧም ይታወሳል።