ኢሳት (ህዳር 13 ፥ 2009)
የደቡብ ሱዳን አማጺ ቡድን መሪ ሪክ ማቻር በአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ከደረሱ በኋላ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ወደ መጡበት ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲመለሱ ማድረጋቸው ተገለጸ።
የአማጺ ቡድኑ መሪ ሪክ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት የቡድኑ ጽ/ቤት ዋና መቀመጫ ወደ ሚገኝበትና ከኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ ባለው የደቡብ ሱዳን የፓጋክ ግዛት የመሄድ እቅድ እንደነበራቸው የሱዳን ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ አመራሮች አስታውቀዋል።
ይሁንና ሪክ ማቻር በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በደረሱ ጊዜ ለአንድ ሰዓት ከግማሽ ያህል ጊዜ በቁጥጥር ስር ተደርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲመለሱ አልያም ወደ ደቡብ ሱዳን በሃይል ሊወሰዱ እንደሚችሉ አማራጭ ቀርቦላቸው እንደነበር የአማጺ ቡድኑ ሃላፊዎች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
በአማጺ አመራሩና በኢትዮጵያ ባለስልጣናት በኩል የተካሄደን ድርድር ተከትሎ ሪክ ማቻር በሌላ በረራ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲመለሱ መደረጉን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ የአማጺ ቡድኑ አመራሮችን በምንጭነት በመጥቀስ ዘግቧል።
በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ያካሄደውን ውይይት ተከትሎ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው እንደማይገቡ ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።
ሪክ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ እገዳ ቢጣልባቸውም ወደ ሌላ ሃገር ለሚያደርጉት ጉዞ ኢትዮጵያን ለመሸጋገሪያነት መጠቀም እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማብራሪያን ሰጥቶ እንደነበር መዘገቡ የሚታወቅ ነው።
ይሁንና የአማጺ ቡድኑ መሪ አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ ወደ ፓጋክ ሊያደርጉ የነበረው ጉዞ በምን ምክንያት ሊከለከል እንደቻለ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሰጡት ምላሽ የለም።
በደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የአማጺ ቡድኑ መሪ ሪክ ማቻር ለአንድ አመት ያህል መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ አድርገው ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ድርድር ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ አነሳሽነት በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት አደራዳሪነት የተካሄደውን ይህንኑ ድርድር ተከትሎ ሁለቱ ወገኖች የሰላም ስምምነት የደረሱ ሲሆን፣ ሪክ ማቻር የምክትል ፕሬዚደንትነት ስልጣን እንዲረከቡ ተደርጓል።
ይሁንና ማቻር ከአዲስ አበባ ወደ ጁባ ተጉዘው ስልጣናቸውን ቢረከቡም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በመንግስታቸውና በአማጺ ቡድኑ መካከል በተቀሰቀሰ አዲስ ግጭት ማቻር ወደ ሱዳን መኮበብላቸው የሚታወስ ነው።
ጎረቤት ሱዳን ለአማጺ ቡድኑ መሪ በቂ እንቅስቃሴ ባለመፍቀዷ ምክንያት ማቻር ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
ሪክ ማቻር ከደቡብ አፍሪካ በመነሳት በኢትዮጵያ በኩል ወደ አማጺ ቡድኑ ዋና መቀመጫ ወደ ሚገኝንበት ስፍራ ለማድረግ ያደረጉት ጉዞ ሰኞ መስተጓጎሉን የአማጺ ቡድኑ ሃላፊዎች ይፋ አድርጓል።
ሪክ ማቻር በአዲስ አበባ በነበራቸው የአንድ አመት ቆይታ ልዩ ማረፊያ ተዘጋጅቶላቸው በኢትዮጵያ መንግስት ጥበቃና የተለያዩ ድጋፎች ሲደረግላቸው እንደነበር ይነገራል።
ይሁንና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር የደረሱትን ስምምነት ተከትሎ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ የተደረገ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሃገሪቱ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ችግር ፈጥረዋል ባላቸው አካላት ላይ ማዕቀብ ለመጣል በዝግጅት ላይ መሆኑ ይታወቃል።