ኢሳት (ህዳር 13 ፥ 2009)
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በሃገሪቱ ፕሬዜዳንት ጃኮብ ዙማ ላይ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀረበን የሙስና ቅሬታ ለመመርመር መወሰኑ ተገለጸ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከበርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ተቃውሞ እየቀረበባቸው የሚገኙት ዙማ ስልጣናቸውን በመጠቀም የመንግስት ሃብትን እንደመዘበሩ የደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚ ሃይሎችና ሌሎች የሲቪክ ተቋማት ቅሬታን እያቀረቡ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ከእነዚሁ አካላት የቀረበን የሙስና ቅሬታ ለመመርመር የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ውሳኔ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ፕሬዚደንቱ በስልጣን ላይ እያሉ እንዲህ ያለ ምርመራ ሲካሄድባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ተነግሯል።
የሃገሪቱ ልዩ የሙስናና የወንጀል መርማሪ ቡድን በጃኮብ ዙማ ላይ የሚካሄደውን ምርመራ በቅርቡ እንደሚጀምር የዲሞክራቲክ ጥምረት ፓርቲ አመራር ሙሲ ማይማኒ ለሮይተርስ ገልጸዋል።
ይሁንና በፕሬዚዳንቱ ላይ የሙስና ምርመራን ያካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ልዩ ሃይል በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት መቆጠቡን የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ ገዢው የአፍሪካ ብሄራዊ ምክር ቤት ከደቡብ አፍሪካ ዜጎች ታይቶ የማይታወቅ ህዝባዊ ተቃውሞ እየቀረበበት ሲሆን፣ ባለፈው ነሃሴ ወር በተካሄደ የክልል ምርጫ ፓርቲው በርካታ ዋና ዋና ከተሞች ሽንፈት እንዳጋጠመው ይታወቃል።
በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መወገድን ተከትሎ ለስልጣን የበቃውም ገዢው የአፍሪካ ብሄራዊ ምክር ቤት ድህነትን መቀነስ ባለመቻሉና ሙስናን አስፋፍቷል በሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲቀርብበት ቆይቷል።
ይሁንና ፓርቲው ድርጊቱን ለማስተባበል ቢሞከርም የገዢው ፓርቲ ተዓማኒነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየቀነሰ መምጣቱን የሃገሪቱ የፖለቲካ ተንታኞች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ደቡብ አፍሪካ ከሁለት አመት በኋላ በምታካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ፉክክር ያጋጥማቸዋል ተብሎ ተሰግቷል።
ፕሬዚደንት ዙማ እየቀረበባቸው ያለው የሙስና ቅሬታን ተከትሎ የሃገሪቱ የተቃዋሚ ፓሪቲዎች ፕሬዚደንቱ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንዲለቁ ሲጠየቁ ቆይተዋል።