በደቡብ ኦሞ  ዞን ጂንካ ከተማ የተጠራው ስብሰባ ሳይሳካ ቀረ

ኅዳር ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን በጂንካ ከተማ የኢህአዴግ አባልና ደጋፊ የመንግሥት ሠራተኞችን ለይተው ‹‹በወቅታዊ ጉዳዮች›› ላይ ለማወያየት የተጠራው ስብሰባ ሠራተኛው በስብሰባው ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሳይሳካ መቅረቱን የከተማው ሠረተኞች ገልጸዋል፡፡

ዛሬ ሰኞ ህዳር 12/2009 ዓ.ም ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ ወደ ሥራ ገበታው ሲገባ የቢሮ ኃላፊዎች  የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች የሆኑትን ሠራተኞች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለማወያየት ፕሮግራም ስለያዘ ወደከተማው ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ እንሄዳለን በማለት ወደዚያው እንዲሄዱ ያዛሉ፡፡ ሠራተኛው ከቢሮው እንደወጣ በመንገድ ላይ ከፊሉ ወደቤቱ፣ ከፊሉ ወደቤተክርስቲያን ቀሪውም ወደጉዳዩ በማምራቱ በአዳራሹ የተገኘው ቁጥር ከሰራተኛው ሩብ የማይሞላ በመሆኑ የዞን መስተዳድር ባለሥልጣናትና የኢህአዴግ ከፍተኛ ካድሬዎች በመበሳጨት ‹‹አሁን የተገኛችሁ ከሰዓት እንዳትቀሩ ፣በዚህ ቁጥር ስብሰባ ማካሄድ ስለማንችል ስብሰባው ለከሰዓት በኋላ ተላልፏል›› ብለው ያሰናብታሉ፡፡

ከሰዓት በኋላ የዞኑ መንግስትና የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ከአዳራሹ ቀድመው ቢደርሱም ጠዋት የተገኘውን ያህል ቁጥርም ባለመገኘቱ እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሠዓት በግቢው ውስጥ ሲንጎራደዱ ቆይተው  በብስጭት ወደየቢሮኣቸው መበተናቸውን ሁኔታውን የተከታተሉና በጠዋቱም በከሰዓት በኋላም በስብሰባ ቦታው የተገኙ ሰራተኞች  ከሥፍራው ገልጸውልናል፡፡

ኢሳት ባለፈው ሳምንት በጂንካ ከተማ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ፡-

1.መምህር ዓለማዬሁ መኮንን – የኦሞ ህዝቦች ዲ/ዊ ኅብረት (ኦህዲኅ) ም/ሊ/መንበርና የዞን ተጠሪ፤

2.መምህር ኢንድሪስ መናን -የኦህዲኅ የዞን  ም/ሰብሳቢ፤

3.ወጣት  ዳዊት ታመነ– የኦህዲኅ ዞን ስራ አስፈጻሚ የፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ፤

4.ወጣት መሃመድ ጀማል -የኦህዲኅ ዞን ስራ አስፈጻሚ የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ፤

5.አቶ ሀሪይሁን ኤበዞ  – የኦህዲኅ  አባል ፤እንዲሁም

6.አቶ ስለሺ ጌታቸው – የቀድሞ መኢአድ/አንድነት የዞን ተጠሪ … መታሰራቸውንና እስከ አሁን  ምንም ጥያቄ ያልቀረበላቸው እንዲሁም ስለታሰሩበት ጉዳይ እንዳልተገለጸላቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡