የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው የወጡት በሎጂስቲክ ችግር ምክንያትና ለስልታዊ ዕርምጃ ነው ተባለ

ኢሳት (ኅዳር 12 ፥ 2009)

በሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ቁልፍ ከተባሉ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው የወጡት በሎጂስቲክ ችግር ምክንያትና ለስልታዊ ዕርምጃ መሆኑን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስትሩ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ተወልደ ሙሉጌታ አልሸባብ የተሰኘው የሶማሊያ ታጣቂ ሃይል የኢትዮጵያ ወታደሮች ለቀው የወጡ ስፍራዎችን መያዙ ለመንግስት ስጋት የለውም ሲሉ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

የሶማሊያ ባለስልጣናት እና የተለያዩ አካላት በሃገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ባኩል፣ ሂራን፣ ጋልጋዱድ ከተባሉና ከሌሎች ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው መውጣታቸው ሲገልፁ ቆይተዋል።

በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ምላሽን የሰጠው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርጊቱ ትክክልኛ መሆኑን አረጋግጦ ወታደሮቹ አካባቢውን ለቀው የወጡት በሎጂስቲክ ችግር ምክንያትና ለስልታዊ ዕርምጃ እንደሆነ አመልክቷል።

ይሁንና ቁጥራቸው በትክክል ያልተገለጸው ወታደሮች ስላጋጠማቸው የሎጂስቲክስ ችግርና ስልታዊ ነው ስለተባለው ዕርምጃ ሚኒስቴሩ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።

በሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች እያደረጉ ያለው እንቅስቃሴ ጥንቃቄና ሃላፊነት የተሞላበት በመሆኑ የአልሸባብ መስፋፋት በኢትዮጵያ ላይም ሆነ በአካባቢው ስጋት አይኖረውም ሲሉ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

ይሁንና የኢትዮጵያ ወታደሮች ከቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው መውጣታቸው ለታጣቂ ሃይሉ ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩንና አልሸባብ በሚፈጽመው ጥቃት ሊጨምር ይችላል ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ለአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ አስረድተዋል።

ባለፈው ወር ወታደራዊ ቦታዎቹን ለቀው የወጡት የኢትዮጵያ ወታደሮች አካባቢውን ለአመታት ያህል ይዘው እንደቆዩ የሶማሊያ ባለስልጣናት ይገልጻሉ።

የተለያዩ አካላት ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ የተደረገው በኢትዮጵያ ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ግንኙነት እንዳለው መሆኑን ቢገልጹም መንግስት መረጃውን ሲያስተባብል ቆይቷል።

ባለፈው ሳምንት በደህንነትና በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ሪፖርቶችን ለንባብ የሚያበቃው አፍሪካ ኮንፌዴንሻል መጽሄድ ከሶማሊያ ለቀው የወጡ ወታደሮች ቁጥር ወደ 12ሺ አካባቢ እንደሚገመት መዘገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ወደ አራት ሺ የሚጠጉ ወታደሮች ሶማሊያ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ስር አሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን፣ ቁጥራቸው ያልታወቀ የተናጥል ወታደሮችም በተለያዩ የሶማሊያ ግዛቶች አሰማርቶ እንደሚገኝ ይነገራል።

ይሁንና መንግስት የእነዚህን ወታደሮች ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥቦ ይገኛል። ኢትዮጵያ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከታህሳስ ወር 1999 ጀመሮ ወታደሮቿን በሶማሊያ አሰማርታ እንደምትገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።