አትላስ አፍሪካን ኢንዱስትሪስ ከኢትዮጵያ ለቆ መውጣቱ ተገለጸ

ኢሳት (ኅዳር 12 ፥ 2009)

በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ገንዘብ ያለ አግባብ አግዶብኛል በማለት ቅሬታን ያቀረበ አንድ አለም አቀፍ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ለቆ መውጣቱን ይፋ አደረገ።

አትላስ አፍሪካን ኢንዱስትሪስ የተሰኘው ይኸው ኩባንያ ለራያ ቢራ አፍሪካ የቢራ ምርት ማሸጊያ ጠርሙሶችን ለማምረት ስምምነት አድርጎ የሽርክና ስራ ሲሰራ መቆየቱን አውስቷል።

ይሁንና ኩባንያው የሽክርና ስራው በጀመረ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ገቢዎች ጉምሩክ ባለስልጣን ሽርክና ካደረገው ኩባንያ ያልተጠናቀቀ የታክስ ክፍያ አለ ተብሎ ክፍያ እንዲፈጸም መንገዱን አስታውቋል።

የዚሁ ኩባንያ ሃላፊዎች በመንግስት የተጠየቁት ክፍያ የቀድሞውን የሽርክና አጋር ድርጅት የሚመለከት እንጂ አትላስ አፍሪካን ኢንዱስትሪስን የሚመለከት አይደለም ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸውን ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል።

መቀመጫውን በኬንያ ያደረገው ድርጁት ለመንግስት ያቀረበው አቤቱታ በጎ ምላሽን ሊያገኝ ባለመቻሉ ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ለቆ መውጣቱን ይፋ አድርጓል።

ኩባንያው ከታክስ ክፍያ ጋር ከመንግስት ጋር የገባውን አለመግባባት ተከትሎ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የነበረውን 2.4 ሚሊዮን ዶላር እንዲታገድበት ተደርጎ መቆየቱን የገለጸ ሲሆን፣ ገንዘቡ ይለቀቅለት አልያም አሁንም ድረስ ታግዶ ይሆን የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

ኩባንያው ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ለቆ ለመውጣት መወሰኑን ተከትሎም ተመሳሳይ የኢንቨስትመንት ስራ ላይ ለመሰማራት በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የገበያ ጥናትን እያደረገ እንደሚገኝ ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።

በድርጅቱ ሽርክና የነበራቸው ባለሃብቶች በአሁኑ ወቅት የገበያ ድርሻቸውን በመሸጥ ላይ ሲሆኑ በኢትዮጵያ በሽርክና ስራ በመሰማራቱ የ254ሺ ዶላር አካባቢ ኪሳራ እንደደረሰበት አስታውቋል።

በብሪታኒያ በበርካታ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሰማርቶ የሚገኘው አትላስ አፍሪካን ኢንተርፕራይዝ በኢትዮጵያ ቆይታው ወደ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት ተግባራዊ አድርጎ እንደነበር አውስቷል።

ባለፈው ወር አንድ የእስራዔል የማዕድን ፈላጊ ኩባንያ የኢትዮጵያ መንግስት የገባውን ቃል ተግባራዊ አላደረገም በማለት ከኢትዮጵያ ለቆ መውጣቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

አይ ሲ ኤል (ICL) የተሰኘው ይኸው ኩባንያ በአፋር ክልል ለሚያደርገው የፖታሽ ማዕድን ፍለጋ 170 ሚሊዮን ዶላር መድቦ እንደነበር አስታውቋል።

ይሁንና መንግስት ለማዕድን ፍለጋ ፕሮጄክቱ የመሰረተ-ልማቶችን ለሟሟላት ቃል ቢገባም፣ ምንም ግንባታ ሊያከናውን አልቻለም ሲል ቅሬታውን አቅርቧል።

መንግስት ሁለቱ ኩባንያዎችን ለቀው መውጣታቸውን በተመለከተ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ባለፈው አመት የተባበሩት አረብ ኤመሬት ባለሃብቶች ተመሳሳይ ቅሬታን ሲያቀርቡ መቆየታቸውን መዘገባችን የሚታወቅ ነው።