ከውጭ ንግድ ሊገኝ ከታሰበው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት ተመዘገበ

ኢሳት (ኅዳር 9 ፥ 2009)

በተያዘው አመት ሩብ አመት ከውጭ ንግድ ሊገኝ ከታሰበው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት መመዝገቡን የንግድ ሚኒስቴር አርብ አስታወቀ።

በሩብ አመቱ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ለማግኘት እቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ከውጭ ንግዱ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ወደ 640 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ብቻ መሆኑ ታውቋል።

የምርት ጥራት ጉድለት እንዲሁም በአቅራቢዎችና በላኪዎች እጅ የሚገኝ የግብርናና ሌሎች ምርቶች ወደ ገበያ አለመቅረብ ለእቅዱ አለመሳካት ምክንያት ሆኗል ሲል የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ይሁንና አቅራቢዎችና ላኪዎችን በምን ምክንያት ምርቶቻቸውን ማቅረብ እንዳልቻሉ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ የገቢም መዋዠቅ በውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ ይጠበቃል።

በኦሮሚያ ክልል ለአንድ አመት ያህል ጊዜ የዘለቀውና በቅርቡ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ በሃገሪቱ የውጭ ንግድ ላይ እክል መፍጠሩን የተለያዩ አካላት ሲገልፁ ቆይተዋል።

ባለፈው በጀት አመት መንግስት ከውጭ ንግድ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ለማግኘት እቅድን ቢነድፍም ሊገኝ የቻለው ግን ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ብቻ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

በተያዘው በጀት አመት ተመሳሳይ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት እቅድ የተያዘ ሲሆን፣ በሃገሪቱ ያለውን አለመረጋጋትና የባለሃብቶች ስጋት ገቢው እንዲቀንስ የሚያደርግ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ የታሰበው የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክቷል።