ኢሳት (ኅዳር 9 ፥ 2009)
በኦሮሚያ ክልል ባለፈው አመት የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የኢትዮጵያ የግብርና እድገት ከሶስት በመቶ በላይ ማሽቆልቆሉ ተገለጸ።
በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የውጭ ሃገርና አለም አቀፍ ተወካዮች ጋር ውይይትን ያካሄዱ የመንግስት ባለስልጣናት ባለፈው አመት በኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ዙሪያ ከፍተኛ ችግር ማጋጠሙን አረጋግጠዋል።
ባለፉት 10 አመታት ስምንት በመቶ ሲያድግ ነበር የተባለው የግብርና ዕድገቱ ወደ 2.9 በመቶ ማሽቆልቆሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ አስታውቀዋል።
ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ በሃገሪቱ የውጭ ንግድ ላይ ከፍተኛ ውጭ ምንዛሪ ማስመዝገቡን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።
በተለይ የግብርና ዘርፉ ክፉኛ ጉዳት እንደደረሰበት የሚናገሩት ባለሙያዎች ወደ ተለያዩ ሃገራት ሊላኩ የነበሩ የግብርና ምርቶች በተጠበቀው መጠንና እቅድ ሊቀርብ አለመቻሉን አስረድተዋል።
የግብርና ዕድገት ከሶስት በመቶ እድገት በላይ ማሽቆልቆሉን ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ በተቃራኒው የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፉ በ20 እና በ11 በመቶ እድገት አስመዝግቧል ማለታቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ይሁንና በሃገሪቱ ያለው ፖለቲካው ውጥረትና አለመረጋጋት በኢኮኖሚው ላይ ካደረሰ ተፅዕኖ በተጨማሪ የውጭ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንታቸው ለማጤን እንደተገደዱ የብሪታኒያው ኢንዲፔንደት ጋዜጣ በቅርቡ መዘገቡ ይታወሳል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው በሃገሪቱ ያለው የፖለቲካ ውጥረት በኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያሳደረ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ምላሽን የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትሩ የዘንድሮው የኢንቨስትመንት ፍሰት የተሻለ እንደሚሆን ይገመታል ሲሉ ተናግረዋል።
መንግስት አጠቃላይ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ባለሁለት አሃዝ ያድጋል ሲል ቢቆይም በተጠናቀቀው የ2008 በጀት አመት እድገቱ ስምንት በመቶ ሆኖ መመዝገቡን አቶ ሃይለማሪያም ደሳለን በውይይቱ ወቅት አንስተዋል።
ይሁንና የአለም ባንክ ኢትዮጵያ ባጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የውጭ ንግድ ማሽቆልቆል ምክንያት የኢኮኖሚ እድገቱ ከስድስት በመቶ እንዳማይበልጥ ሲገፅ ቆይቷል።
ሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ለማስጠበቅ አፋጣኝ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግን እንዳለበት የአለም ባንክን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በማሳሰብ ላይ ናቸው።