የአርበኞች ግንቦት7 ሃይል ከህወሃት/ኢህአዴግ ወታደሮች ጋር በቀብትያ ሁመራ እና አጎራባች ቀበሌዎች  እየተዋጋ ነው

ኅዳር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የአርበኞች ግንቦት7 የሰሜን ጎንደር አስተባባሪ እንደገለጹት፣ አባሎቻቸው በሰሜን ጎንደር በተለያዩ አካባቢዎች ለወራት ሲደራጁና ሲያደራጁ ከቆዩ በሁዋላ፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ወታደራዊ ጥቃት በመፈጸም ላይ ናቸው። በተለይ ከትናንት ጀምሮ በቃፍታ ሁመራ እና በአከር አካባቢ ከፍተኛ ውጊያ እያካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።

አደንድን በሚባል አካባቢ ባለፈው ሳምንት በተደረገው ጦርነት 48 የአገዛዙ ወታደሮች መገደላቸውን የገለጹት አስተባባሪው፣ ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንና አንድ የጸረ ሽምቅ ሃላፊ መገደሉን ገልጸዋል። ሃይላቸው ወደ መሃል አገር ለመግባት እየታገለ መሆኑንም ተናግረዋል።

ራሳቸውን በጎበዝ አለቆች አደራጅተው በረሃ ወርደው ሲታገሉ የነበሩትን በማሰባሰብ እና ድጋፍ በማድረግ ወደ አንድነት እንዲመጡ ማድረጋቸውን የገለጹት አስተባባሪው፣ አገሩን ነጻ ለማውጣት የሚፈልግ ሃይል ሁሉ በማንኛውም ጊዜ መጥቶ ሊቀላቀላቸው እንደሚችል ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ 1 ሰአት ላይ በደረሰን መረጃ ደግሞ በሁለቱ ሃይሎች መካከል ከፍተኛ ጦርነት ሲካሄድ ከዋለ በሁዋላ፣ አርበኞቹ ከርሰሌት በሚባለው ቦታ ላይ የሚገኘውን አደባይ ተራራን መቆጣጠራቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል። የመጀመሪያው ጥቃት በአዲ ጎሹና ሁመራ መካከል በምትገኘው እንድሪስ አካባቢ መፈጸሙ የታወቀ ሲሆን፣ በእዚሁ አካባቢ በነበሩ የገዢው ፓርቲ ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ከአርበኞች ግንቦት 7 በኩል 3 ሰዎች መስዋት መሆናቸውንም ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከሰአት በሁዋላ በ52 መኪኖች የተጫኑ ወታደሮች በሽሬ ፣አድርቃይ፣ ማይጸብሪ፣ ጸለምት አድርገው ታጋዮችን ለመግጠም የተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ በዳንሻ አካባቢም በ8 መኪኖች የተጫኑ ወታደሮቸ ሰፍረዋል። ታጋዮቹ ወደ ጠገዴ፣ አርማጭሆ ፣ ቆላ ወገራና ሌሎችም አካባቢዎች ሰንጥቀው ከገቡ ከህዝብ ጋር በመቀላቀል ወደ መሃል ይገሰግሳሉ የሚል ስጋት የገባው አገዛዙ፣ ለትግራይ አካባቢ ህዝብና ሚሊሺዎች “ አርበኞች ግንቦት7 መጥቷልና ራሳችሁን አድኑ “ በማለት ሲቀሰቅስ፣ ለአማራ ተወላጆች ደግሞ “ሽፍቶች ገብተዋል”ና ተነሱ እያለ ነው። በገዢው ፓርቲ በኩል እስካሁን የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም።