ኢሳት (ህዳር 8 ፥ 2009)
የአለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) ኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆዎርናሊስትስ የኢትዮጵያ መንግስት ለእስር የዳረጋቸውን ሁሉም ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈታ ሃሙስ ጥሪውን አቀረበ።
በሃገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ወከባ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ድርጅቱት ለመንግስት ባቀረበው የጸሁፍ መልዕክት አመልክቷል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ አንድ ጋዜጠኛን ጨምሮ ሁለት ጦማሪያን ለእስር መዳረጋቸውን ያወሳው ሲፒጄ ሌላ አንድ ጋዜጠኛ የገባበት አለመታወቁን አክሎ ገልጿል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለይ በጋዜጠኞችና በጦማሪያን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ሲሉ የድርጅቱ የአፍሪካ ክፍል አስተባብሪ የሆኑት አንጀላ ኪንታል ተናግረዋል።
በቅርቡ ለእስር የተደደረጉት ጦማሪያን ጋዜጠኞች ምንም ክስ እንዳልተመሰረተባቸው ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ከአንድ ሳምንት በላይ የገባበት ያልታወቀው ጋዜጠኛ አብዲ ገዳ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ሊሆን ይችላል ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ለጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋሙ ገልጸዋል።
ድርጅቱ ለመንግስት ያቀረበው ጥያቄ አስመልክቶ አዲስ ለተሾሙት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስቴር አቶ ነገሪ ሌንጮን ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም እንዳልተሳካለት በጽሁፉ አስፍሯል።
ሲፒጄ በፈረጆቹ 2015 ዓም ባወጣው አመታዊ ሪፖርት ኢትዮጵያ በአለም በመገናኛ ብዙሃን ላይ የከፋ አፈናን ይፈጽማሉ ብሎ ከፍረጃቸው 10 አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት ከ10 የሚበልጡ ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገው የሚገኙ ሲሆን፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያኑ የስቃይ ሰለባ ይሆናሉ ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅቶች ስጋታቸውን እየገለጽ ይገኛል።