ኢሳት (ህዳር 8 ፥ 2009)
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአፍሪካ ሃገራት ከአለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባልነት ለመውጣት እያካሄዱ ያለውን ዘመቻ አወገዘ። የአህጉሪቱ ሃገራት ከአባልነት ለመውጣት እየወሰዱ ያለው እርምጃ ከተጠያቂነት በማምለጥ የተያዘ ስልት ነው ሲሉ የኮሚሽኑ ሃላፊ ዘይድ ራድ አል ሁሴን ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መግለጻቸውን ቢቢሲ ሃሙስ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በተለያዩ ጊዜያት በአዲስ አበባ በመሰብሰብ አህጉሪቱ በአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ያላትን ድርሻ እንድትመረምር ጥሪን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አባል ሃገራት መካከል ሲካሄድ የቆየውን ይህንኑ ውይይት ተከትሎ ቡሩንዲ፣ ጋምቢያ እና ደቡብ አፍሪካ ከአባልነት ለመሰናበት ውሳኔን አስተላልፈዋል።
ይሁንና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሃገራቱ የወሰዱት ዕርምጃ በአፍሪካ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአለም አቀፉ ደረጃ ትኩረት እንዳያገኙና ከተጠያቂነት ለማምለጥ ነው ሲል ድርጊቱን አውግዟል።
ሃገሪቱ እየወሰዱት ያለው ዕርምጃ በመርህ ላይ የተመሰረተ አይደለም ያሉት የኮሚሽኑ ሃላፊ ዘይድ ራድ ውሳኔን የአፍሪካ መሪዎችን ተጠያቄ ላለማድረግ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ናይጀሪያ በበኩሏ የፍርድ ቤቱን ተልዕኮ በመደገፍ ድጋፏን ያሳየች ሲሆን፣ ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበትነት እየተወዳደሩ የሚገኙ የቦትስዋና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፔሎሚኒ ቤንሰን አፍሪካ ከፍርድ ቤት መሰናበት እንደሌለበት አቋማቸውን ይፋ አድርጓል።
የአፍሪካ ሃገራት ከፍርድ ቤቱ ከመሰናበት ይልቅ ተባብረው ሲሰሩ የተሻለ መግባባት ይኖራል ሲሉ ሚኒስትሯ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና የፖለቲካ ተንታኞች ሚንስትሯ የያዙት አቋም ለሊቀመንበርነት ለመወዳደር በያዙት ሂደት ላይ ተጽዕኖን ሊያሳድርባቸው ይችላል በማለት ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛል።
የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት ከሁለት ወር በኋላ በአዲስ አበባ በሚያካሄዱት አመታዊ ጉባዔ ለቀጣዩ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።